በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
5፥14 ከእነዚያም "እኛ "ነሷራ" ነን" ካሉት የጠበቀ ቃል ኪዳናቸውን ያዝን፡፡ በእርሱም ከታዘዙበት ነገር ፈንታን ተውት፡፡ وَمِنَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّا نَصَارَىٰ أَخَذْنَا مِيثَاقَهُمْ فَنَسُوا حَظًّا مِّمَّا ذُكِّرُوا بِهِ
ኢየሱስ ለጴጥሮስ፦ "የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል" ብሎታል፦
ማቴዎስ 16፥19 የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።
ጴጥሮስ የኢየሱስ ተተኪ፣ ወኪል፣ እንደራሴ ነው፥ ጴጥሮስ ከኢየሱስ እንዲህ ያለ ሥልጣን ስለተቀበለ በሐዋርያት መካከል ሊቀ መንበር ነው፥ "ካቴድራ" καθέδρα ማለት "ወንበር" ማለት ነው፦
ማቴዎስ 23፥2 ጻፎች እና ፈሪሳውያን በሙሴ “ወንበር” ተቀምጠዋል። λέγων Ἐπὶ τῆς Μωϋσέως καθέδρας ἐκάθισαν οἱ γραμματεῖς καὶ οἱ Φαρισαῖοι.
እዚህ አንቀጽ ላይ "ወንበር" ለሚለው የገባው ቃል "ካቴድራስ" καθέδρας ሲሆን "ካቴድራል"cathedral" የሚለው ቃል እራሱ "ካቴድራስ" ከሚል የመጣ ነው፥ በግዕዝ "መንበር" ይባላል። "ፔትሮስ" Πέτρος ማለት "ዓለት" ማለት ነው፥ ኢየሱስ ጴጥሮስን፦ "ዓለት ነህ" "በዚህ ዓለት ላይ ኤክሌሲያ እሠራለው" ብሏል፦
ማቴዎስ 16፥18 እኔም እልሃለሁ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚህም ዓለት ላይ ቤተ ኤክሌሲያዬን እሠራለሁ፥ የሲዖል ደጆችም አይችሉአትም። κἀγὼ δέ σοι λέγω ὅτι σὺ εἶ Πέτρος, καὶ ἐπὶ ταύτῃ τῇ πέτρᾳ οἰκοδομήσω μου τὴν ἐκκλησίαν, καὶ πύλαι Ἅιδου οὐ κατισχύσουσιν αὐτῆς.
የጴጥሮስ የተጸውዖ ስሙ "ስምዖን" ሲሆን "ጴጥሮስ" ግን የማዕረግ ስሙ ነው፥ በዐረማይስጥ "ኬፋ" ܟ݁ܺܐܦ݂ܳܐ ማለት እራሱ "ዐለት" ማለት ነው። በጴጥሮስ ዐለትነት ላይ የተመሠረተችው ጉባኤ "የሲዖል ደጆችም አይችሉአትም" ተብሏል። "ኤክሌሲያ" ἐκκλησία የሚለው የግሪኩ ቃል ከሁለት ቃላት የተዋቀረ ቃል ነው፥ እርሱም "ኤክ" ἐκ ማለትም "ከ" ከሚል መስተዋድድ እና "ካሌኦ" καλέω ማለትም "የተጠራ" ከሚል ግስ ነው። በጥቅሉ "ተጠርተው የወጡ" ማለት ነው፥ ይህ ቋንቋዊ ፍቺው ሲሆን ሙያዊ ፍቺው ደግሞ "ጉባኤ" "ማኅበር" "ስብሰባ" ማለት ነው። ኢየሱስ በጴጥሮስ "እሠራለው" ያለው ስብስብ "ኤክሌሲያ" ተብሏል፥ ጴጥሮስም እንዲህ ብሏል፦
ቀለሜንጦስ 10፥4 "እኔ ጴጥሮስ መንፈሳዊ አባታችሁ ነኝ፥ በዚህ የሾመኝ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። "ዓለት" ተብዬ በእርሱ ዘንድ ተሹሜአለው፥ እናንተ በእኔ መሠረታት ላይ ትታነጹ ዘንድ እኔም በተሰጠኝ ችሎታ ይህንን ሠራሁኝ"።
ይህችን ኤክሌሲያ "ካቶሊክ" ያላት የአንጾኪያው ኤጲስ ቆጶስ አግናጥዮስ በ 110 ድኅረ-ልደት ነው፥ "ክርስትና" የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ያመጣው ይህ ሰው ነው። በሮም የሞተው የአንጾኪያው ኤጲስ ቆጶስ አግናጥዮስ ለሰርምኔስ በጳፈው ደብዳቤ በግሪኩ "ካቶሊኮስ" καθολικός የሚል ቃል የተጠቀመ ሲሆን ትርጉሙ "ዓለም ዐቀፍ" በግዕዝ "ኲላዊት" በሮማይስጥ "ካቶሊክ" ነው።
የፈረንሳዩ ኤጲስ ቆጶስ ሔራንዮስ በ 180 ድኅረ-ልደት ላይ "እውነታው ያለው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንጂ ሌላ በየትም አይደለም" ብሏል፦
የምንፍቅናዎች ተቃውሞ 3፥4 "እውነታው ያለው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንጂ ሌላ በየትም አይደለም"።
Against heresies 3፥4 "The truth is to be found nowhere else but in the Catholic Church".
ሮም ውስጥ የጴጥሮስ መንበር ሲኖር የኒቂያ ጉባኤም በ 325 ድኅረ ልደት "የሮሙ የጴጥሮስ በዓለ መንበር ሐዋርያት እንዳዘዙ አለቃም ፈራጅም ይሁን" በማለት አዘዙ፦
ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 4 ቁጥር 40
"ሊቃነ ጳጳሳት በዓለም ሁሉ አራት ብቻ እንዲሆኑ በኒቂያ የተሰበሰቡት የቅዱሳን ማኅበር አዘዙ። ከእነርሱም የሮሙ የጴጥሮስ በዓለ መንበር ሐዋርያት እንዳዘዙ አለቃም ፈራጅም ይሁን"።
በመቀጠል የኒቂያ ጉባኤ ሊቀ ጳጳስን "ካቶሊኮስ በሚባል ታላቅ ስም ያክብሩት" በማለት ተናግረዋል፦
ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 4 ቁጥር 43
"ካቶሊኮስ በሚባል ታላቅ ስም ያክብሩት"
በጴጥሮስ መንበር ላይ የሚቀመጥ ሐዋርያዊ መተካካት"apostolic succession" ያለው ጳጳስ በክርስቲያኖች አለቆች እና በሰዎች ማኅበር ላይ ሥልጣን እንዳለው እንደ ጴጥሮስ አለቃ ነውና። እርሱ በሕዝቡ እና በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ የክርስቶስ ምትክ ነው ተብሏል፦
ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 4 ቁጥር 54
"እርሱ በክርስቲያኖች አለቆች እና በሰዎች ማኅበር ላይ ሥልጣን እንዳለው እንደ ጴጥሮስ አለቃ ነውና። እርሱ በሕዝቡ እና በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ የጌታችን የክርስቶስ ምትክ ነው"።
ይህንን የሥልጣን ቦታ በመያዝ በቀጣይነት ጴጥሮስን የሚተኩ ሰዎች በትውፊት "ክርስቶስ ደንግጓል" ብለው ተተኪዎቹ የሮማ ጳጳሳት ናቸው፦
“ይህንን የሥልጣን ቦታ በመያዝ በቀጣይነት ጴጥሮስን የሚተኩ ሰዎች መኖር እንዳለባቸው ክርስቶስ ደንግጓል፤ ተተኪዎቹ ደግሞ የሮማ ጳጳሳት ናቸው።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ (2003) ጥራዝ 11፣ ገጽ 495-496
በካቶሊክ ትውፊት ከጴጥሮስ ጀምሮ እስከ ዛሬ 366 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እየተተካኩ መጥተዋል ብለው ያምናሉ፥ ሠለስቱ ምዕት ማለትም ኒቂያ ላይ የተሰበሰቡት 318 ጳጳጳት የጴጥሮስን መንበር የማይቀበል በሲኖዶክስ እንዲወገድ አዘዋል፦
ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 4 ቁጥር 42
"ይህቺ የሠራናትን ሕግ ያፈረሰውን ሲኖዶስ ያወግዘዋል"።
"ሲኖዶስ" σύνοδος ማለት "ጉባኤ" "ስብሰባ"council" ማለት ነው። ይህ የጴጥሮስ መንበር በ451 ድኅረ ልደት በኬልቄዶን ሲኖዶስ የጽብሓውያን አብያተ ክርስቲያናትን"oriental churches" አውግዟል፥ በመቀጠል ይህ የጴጥሮስ መንበር በ 1053 ድኅረ ልደት በሲኖዶስ የመለካውያን አብያተ ክርስቲያናትን"eastern churches" አውግዟል። የጽብሓውያን እና የመለካውያን ስለተወገዙ "ጵጵስናቸው የኑፋቄ ነው" ብለው ያምናሉ፥ ምክንያታቸው "የጴጥሮስን ሰንሰለት የጠበቀ ሐዋርያዊ መተካካት እና ትውፊት በትክክል እኛ ጋር ነው" ያለው የሚል ክፉኛ ሙግት አላቸው።
ዛሬ በዓለም ላይ ከ1.3 ቢሊዮን ምእመናን ያቀፈው ጉባኤ ሮም መቀመጫ ያረገ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ነው፥ በ 381 የቆስጠንጥኒያ ጉባኤ አንቀጸ እምነቱ እንዲህ ነበረ፦
፨በግሪክ፦ "Εἰς μίαν, ἁγίαν, καθολικὴν καὶ ἀποστολικὴν Ἐκκλησίαν"·
፨በኢንግሊሽ፦ "we believe in one, holy, Catholic and Apostolic Church".
፨በዐማርኛ፦ "በአንዲት፣ ቅድስት፣ ካቶሊካዊት እና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን"
"ካቶሊኮን" καθολικὴν የጴጥሮስ መንበር የያዘ የሮማ መቀመጫ የሆነው "ሐዋርያዊ መተካካት ነው" ብለው ያምናሉ። ይህቺ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ናት እንግዲህ በታሪክ ላይ በጦርነት፣ በባርያ ንግድ፣ በቅኝ ግዛት ስትበድል እና ስትገድል የኖረችው፥ ግዝት እና ግዞት የእጇ በመሆን የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ዋንጫውን ወስዳለች።
ይህንን የክርስትና ታሪካዊ ሥነ መለኮት ወደ ቁርኣን ገብተን ስንመዝን ዒሣ ከአይሁዳውያን ክህደት በተሰማውም ጊዜ፡- «ወደ አላህ "ረዳቶቼ" እነማን ናቸው?» አለ፥ ሐዋርያትም፡- «እኛ የአላህ "ረዳቶች" ነን" አሉ፦
3፥52 ዒሣ ከእነርሱ ክህደት በተሰማውም ጊዜ፡- «ወደ አላህ "ረዳቶቼ" እነማን ናቸው?» አለ፥ ሐዋርያትም፡- «እኛ የአላህ "ረዳቶች" ነን፤ በአላህ አምነናል፤ እኛም ትክክለኛ ታዛዦች መኾናችንን መስክር» አሉ፡፡ فَلَمَّآ أَحَسَّ عِيسَىٰ مِنْهُمُ ٱلْكُفْرَ قَالَ مَنْ أَنصَارِىٓ إِلَى ٱللَّهِ ۖ قَالَ ٱلْحَوَارِيُّونَ نَحْنُ أَنصَارُ ٱللَّهِ ءَامَنَّا بِٱللَّهِ وَٱشْهَدْ بِأَنَّا مُسْلِمُونَ
"አንሷር" أَنصَار ማለት "ረዳት" ማለት ሲሆን ሐዋርያት፦ "እኛ አንሷር ነን" ብለዋል፥ እዚህ አንቀጽ ላይ "ታዛዦች" ለሚለው የገባው ቃል "ሙሥሊሙን" مُسْلِمُون መሆኑን ልብ አድርግ! አምላካችን አሏህ " "እኛ "ነሷራ" ነን" ካሉት ከሐዋርያት ጋር የጠበቀ ቃል ኪዳንን ይዟል፦
5፥14 ከእነዚያም "እኛ "ነሷራ" ነን" ካሉት የጠበቀ ቃል ኪዳናቸውን ያዝን፡፡ በእርሱም ከታዘዙበት ነገር ፈንታን ተውት፡፡ وَمِنَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّا نَصَارَىٰ أَخَذْنَا مِيثَاقَهُمْ فَنَسُوا حَظًّا مِّمَّا ذُكِّرُوا بِهِ
"ነስራኒይ" نَصْرَانِيّ የሚለው ቃል "ነሰረ" نَصَرَ ማለትም "ረዳ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ረዳት" ማለት ነው፥ "ነሷራ" نَصَارَىٰ ደግሞ የነስራኒይ ብዙ ቁጥር ሲሆን "ረዳቶች" ማለት ነው። ከሐዋርያት ሕልፈት በኃላ ግን በእነርሱ እግር ሥር ተተካን የሚሉት ነሷራ ከታዘዙበት ነገር ፈንታን ተውት፥ በተውሒድ ላይ ተሥሊሥ በመጨመር እንዲሁ ተሠግዎት፣ ምንኩስና ወዘተ... የሚባል የፓጋን ትምህርት በመጨመር ወሰን አለፉ፦
4፥171 እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፡፡ በአላህም ላይ እውነትን እንጅ አትናገሩ፡፡ يَا أَهْلَ الْكِتَابِ لَا تَغْلُوا فِي دِينِكُمْ وَلَا تَقُولُوا عَلَى اللَّهِ إِلَّا الْحَقَّ
4፥171 «ሦስት ነው» አትበሉ! ተከልከሉ! ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና፡፡ አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ وَلَا تَقُولُوا ثَلَاثَةٌ ۚ انتَهُوا خَيْرًا لَّكُمْ ۚ إِنَّمَا اللَّهُ إِلَـٰهٌ وَاحِدٌ
57፥27 "የፈጠሩዋትንም ምንኩስና በእነርሱ ላይ አልጻፍናትም" وَرَهْبَانِيَّةً ابْتَدَعُوهَا مَا كَتَبْنَاهَا عَلَيْهِمْ
እነዚህ አበው የዒሣን ትምህርት ከግሪክ ወሮም ፍልስፍና፣ ወግ፣ ዐረማዊነት ጋር ቀይጠዋል፥ ወራት እና ሳምንት በጣዖታት ስም መሆናቸው በራሱ ይህ የቅሰጣ ውጤት ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ በመካከላቸው ጠብ እና ጥላቻ መኖሩ የአሏህ ቅጣት ነው፦
5፥14 ስለዚህ እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ በመካከላቸው ጠብንና ጥላቻን ጣልንባቸው፡፡ አላህም ይሠሩት የነበሩትን ሁሉ በእርግጥ ይነግራቸዋል፡፡ فَأَغْرَيْنَا بَيْنَهُمُ الْعَدَاوَةَ وَالْبَغْضَاءَ إِلَىٰ يَوْمِ الْقِيَامَةِ ۚ وَسَوْفَ يُنَبِّئُهُمُ اللَّهُ بِمَا كَانُوا يَصْنَعُونَ
"ስለዚህ" ማለት በእርሱም ከታዘዙበት ነገር ፈንታን በመተዋቸው የምሥራቅ ክርስቲያን እና የምዕራብ ክርስቲያን ጋር፣ የምሥራቁ ከምሥራቅ ጋር፣ የምዕራቡ ከምዕራቡ ጋር እርስ በእርስ በመካከላቸው ጠብ እና ጥላቻ መኖሩ የአሏህ ቁጣ ነው። "መሢሒይ" مَسِيحِيّ ወይም "መሢሒያህ" مَسِيحِيَّة ጠላቶቻቸው ያወጡላቸው የለበጣ እና የሽሙጥ ስም ሲሆን "ቅቡዓዊ" "ቅቡዓን" "መሢሕያዊ" "መሢሐውያን" "ክርስቶሳዊ" "ክርስቶሳውያን" ማለት ነው፦
የሐዋርያት ሥራ 11፥26 ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ። التَّلَامِيذُ مَسِيحِيِّينَ لِأوَّلِ مَرَّةٍ فِي أنطَاكِيَّةَ
እዚህ አንቀጽ ላይ "ክርስቲያን" ለሚለው የገባው ቃል "መሢሒዪን" مَسِيحِيِّينَ ሲሆን "መሢሒይ" مَسِيحِيّ ለሚለው ብዙ ቁጥር ነው፥ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሳምኬት በሚባለው ክፍል ገጽ 550 ላይ "ክርስቲያን" ማለት "ቅቡዕ(የተቀባ) ቅቡዓዊ መሢሓዊ" ማለት እንደሆነ ገልጸዋል። ክርስቲያኖች ሆይ! እውን ክርስቶሶች ናችሁን? አሏህም የዒሣን ተከታዮች "መሢሒዪን" مَسِيحِيِّينَ አላላቸው።
አሏህ ለቅኖች ሂዳያህ ይስጣቸው! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
ወሠላሙ ዐለይኩም
ክርስትና