በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
3፥71 «የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! እውነቱን በሐሰት ለምን ትቀላቅላላችሁ? እውነቱንም እናንተ የምታውቁ ስትኾኑ ለምን ትደብቃላችሁ?» يَا أَهْلَ الْكِتَابِ لِمَ تَلْبِسُونَ الْحَقَّ بِالْبَاطِلِ وَتَكْتُمُونَ الْحَقَّ وَأَنتُمْ تَعْلَمُونَ
ጥንት የነበሩት የፈጣሪ ነቢያት በአምላክ ተልከው ትንቢት ሲመጣላቸው የሚናገሩት በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ነበር፦
2ኛ ጴጥሮስ 1፥21 ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በአምላክ ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።
"በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ" እንጂ "በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ጻፉ" አይልም፥ ብዙ ሰዎች ጳውሎስ የጻፋቸውን አሥራ አራት ደብዳቤዎች"letters" "በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ ነው" ይላሉ። ቅሉ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ የተጻፈ ጽሑፍ የለም፥ ባይሆን በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የተናገሩት ንግግር አለ። ይህም ከአምላክ ተልከው ትንቢት እንጂ ታሪክ አይደለም፥ ከመነሻው ይህ ጥቅስ ስለ ነቢያት እንጂ ስለ እነ ጳውሎስ ሽታው የለውም።
ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ከጥንት ነቢያት ሲጠቅስ ስለሚሳሳት የሚጽፈው በመንፈስ ቅዱስ በጭራሽ አይደለም፦
1ኛ ቆሮንቶስ 2፥9 ነገር ግን፦ "ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው አምላክ ለሚወዱት ያዘጋጀው" ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን።
በብሉይ ኪዳን "ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው" ተብሎ የተጻፈ በባትሪ ብትፈልጉ አታገኙም፥ ጥቅሱን የወሰደበት ቦታ አምላክ ስላዘጋጀው ነገር ሳይሆን አሐዳውያን ባዕድ አምላክን መስማት፣ መቀበል እና ማየት እንዳልፈለጉ የሚያስጨብጥ ነው፦
ኢሳይያስ 64፥4 ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም በጆሮአቸውም አልተቀበሉም ዓይንም አላየችም።
ጳውሎስ ሲኮርጅ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ቢሆን ኖሮ በትክክል ማስቀመጥ ያቅተዋልን? እንቀጥል! ጳውሎስ ከኢሳይያስ ጠቅሶ እንዲህ ይሳሳታል፦
ሮሜ 11፥26 እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ "መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል፥ ከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳል።
ኢሳይያስ 59፥20 ለጽዮን ታዳጊ ይመጣል፥ በያዕቆብም ዘንድ ከኃጢአት ለሚርቁ፥ ይላል ያህዌህ። וּבָ֤א לְצִיֹּון֙ גֹּואֵ֔ל וּלְשָׁבֵ֥י פֶ֖שַׁע בְּיַֽעֲקֹ֑ב נְאֻ֖ם יְהוָֽה
"ለጽዮን ታዳጊ ይመጣል" ማለት እና "መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል" ማለት ሁለት የተለያየ ቃላት ነው፥ "በያዕቆብም ዘንድ ከኃጢአት ለሚርቁ" ማለት እና "ከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳል" ማለት ሁለት የተለያየ ቃላት ነው። መንፈስ ቅዱስ ይህ ጠፍቶት ነው? ጳውሎስ የኮረጀው ከዕብራይስጡ ሳይሆን ከግሪክ ሰፕቱጀንት ነው፦
καὶ ἥξει ἕνεκεν Σιὼν ὁ ῥυόμενος καὶ ἀποστρέψει ἀσεβείας ἀπὸ ᾿Ιακώβ.
ግሪክ ሰፕቱጀንት የዕብራይስጥ ቅጂ ሳይሆን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ የትርጉም ሥራ ነው፥ ጳውሎስ ከትርጉም ሥራ ላይ እየኮረጀ "የአምላክ መገለጥ ነው" ብሎ መቅጠፉ ጥሩ አይደለም። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት የኩረጃ ስህተቶችን የተሳሳተባቸው በቁና ማቅረብ ይቻል ነበር፥ ቅሉ እና ጥቅሉ ግን አንባቢያንን ማሰልቸት ነው።
የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! ከአምላክ የመጣውን እውነት ከኩረጃ ንግግር ጋር ለምን ትቀላቅላላችሁ? ይህ ሥራ ዋጋ ያስከፍላል፦
3፥71 «የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! እውነቱን በሐሰት ለምን ትቀላቅላላችሁ? እውነቱንም እናንተ የምታውቁ ስትኾኑ ለምን ትደብቃላችሁ?» يَا أَهْلَ الْكِتَابِ لِمَ تَلْبِسُونَ الْحَقَّ بِالْبَاطِلِ وَتَكْتُمُونَ الْحَقَّ وَأَنتُمْ تَعْلَمُونَ
አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
ወሠላሙ ዐለይኩም