ከርሱ የሆነ መንፈስ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡ (አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

ከርሱ የኾነ መንፈስ፡-

እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፤ በአላህም ላይ እውነትን እንጂ አትናገሩ፤ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ፣ የአላህ መልክተኛ፣ ወደ መርየም የጣላት (የሁን) ቃሉም ከርሱ የሆነ መንፈስም ብቻ ነው…

ሱረቱ-ኒሳእ 4፡171

ባለፈው ‹‹ከርሱ በሆነው ቃል›› የሚለውን አንስተን፡ በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ብዥታዎችን በአላህ ፈቃድ ለማጥራት የተወሰነ ሙከራ ተደርጓል፡፡ ዛሬም የአላህ ፈቃዱ ከሆነ ‹‹ከርሱ የሆነ መንፈስ›› በሚለው ላይ መጠነኛ ቆይታ እናደርጋለን ኢንሻአላህ፡፡

አንዳንድ ወገኖች እንደልማዳቸው ይህንን የቅዱስ ቁርኣን ጥቅስ በመጥቀስ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ከአላህ ዘንድ የወጣ መንፈስ ነው ይሉናል (ተዓለሏሁ አምማ የሲፉሁ-ዟሊሙን)፡፡ እስኪ ትክክለኛ ፍቺውንና እርምቱን እንከታተል፡-

1ኛ. ሰዎች በሕይወት ለመኖርና ለመቆየት የሚያስችላቸው ኃይል ‹‹ሩሕ›› (መንፈስ) ይባላል፡፡

ይህ ሩሕ ከሰውነታቸው በወጣና በተለየ ጊዜ የሞተ አካል (በድን) ይሆናሉ፡፡ ያለ ሩሕ ህይወት የለም፡፡ ይህ ሩሕ እጅግ ረቂቅና በአይን የማይታይ በመሆኑ፡ ስለ ምንነቱ ዝርዝር ገለጻ መስጠት አንችልም፡፡ የሱ ዕውቀት አልተሰጠንምና፡፡ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-

“ከሩሕም ይጠይቁሃል፤ ሩሕ ከጌታዬ ነገር (በዕውቀቱ የተለየበት ነገር) ነው ከዕውቀትም ጥቂትን እንጂ አልተሰጣችሁም፤ በላቸው።”(ሱረቱል ኢስራእ 17፡85)

2ኛ. ወደ መርየም ልጅ ወደ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ጉዳይ ስንመጣም የምናገኘው ይህንኑ እውነታ ነው፡፡

አላህ እሱንም ህያው ፍጥረት እንዲሆን በሻ ጊዜ በመርየም ማኅፀን ይህ ሩሕ (መንፈስ) እንዲነፋባት (እፍ እንዲባልባት) ፈቃዱ ሆነ፡፡ በመላኢካው ጂብሪል አማካኝነት የአላህ መለኮታዊ ትእዛዝ ተፈጸመ፡፡ ዒሳም የአደም ልጅ ሰው ሁኖ ተወለደ፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ያስተምራል፡-

“በመጽሐፉ ዉስጥ መርየምንም ከቤተ ሰቧ ወደ ምሥራቃዊ ስፍራ በተለየች ጊዜ (የኾነዉን ታሪኳን) አዉሳ። ከነሱም መጋረጃን አደረገች፣ መንፈሳችንንም (ጂብሪልን) ወደርሷ ላክን፤ ለርሷም ትክክለኛ ሰው ሆኖ ተመሰለላት።፦ እኔ ከአንተ በአልረሕማን እጠበቃለሁ፤ ጌታህን ፈሪ እንደ ኾንክ፣ (አትቅረበኝ) አለች።፦ እኔ ንጹሕን ልጅ ለአንቺ ልሰጥሽ፣ የጌታሽ መልክተኛ ነኝ አላት። (በጋብቻ) ሰዉ ያልነካኝ ኾኜ፣ አመንዝራም ሳልኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል! አለች። ፦ አላት (ነገሩ) እንደዚህሽ ነው ፤ ጌታሽ፦ እርሱ በእኔ ላይ ገር ነው፤ ለሰዎችም ታምር፣ ከኛም ችሮታ ልናደርገው (ይህንን ሠራን) የተፈረደም ነገር ነዉ አለ፤ (ነፋባትም)።”(ሱረቱ መርየም 19፡16-21)

3ኛ. ይህን መንፈስ አላህ ‹‹ከርሱ የኾነ መንፈስ›› ብሎ መጥራቱ፡ ከአላህ ሀልዎት የወጣ፡ ክፋይ ማለት ሳይሆን፡ ግኝቱ ከአላህ የሆነ፡ አላህ የፈጠረውና ያስገኘው ማለት ነው፡፡

ወደራሱ በማስጠጋት ‹‹ከርሱ የሆነ›› ማለቱ፡ ከአላህ የተከፈለና የወጣ ነው ለማለት በፍጹም አይቻልም፡፡ አላህ መንፈስ አይደለምና፡፡ ባይሆን እሱ የመንፈስ ፈጣሪና አስገኚ እንጂ፡፡

“ለናንተም በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ በመላ ከርሱ ሲኾን የገራላችሁ ነው፤ በዚህ ለሚያስተነኑ ሕዝቦች ታምራት አለበት።”(ሱረቱል ጃሲየህ 45፡13)

በዚህ አንቀጽ ውስጥ ጌታ አላህ በሰማያትና በምድር ያሉትን በጠቅላላ ለኛ ያገራልን አምላክ መሆኑን እየገለጸ ነው፡፡ ታዲያ በገለጻው ውስጥ ‹‹ከርሱ ሲኾን›› የሚል ቃል አልለ፡፡ ይህ ማለት፡ ከአላህ ሀልዎት ተቆርሶ ለኛ የተሰጠን ማለት አይደለም (ሱብሐነሁ ወተዓላ አምማ የሲፉሁ-ዟሊሙን)፡፡
ከዛ ይልቅ ‹‹ከርሱ ሲኾን›› ማለት፡- በሰማያትም ሆነ በምድር ያሉ ነገራት በጠቅላላ ፈጣሪያቸውና ባለቤታቸው አላህ ነው፡፡ ምንጭነታቸውም ከሱ ዘንድ ነው ለማለት ነው፡፡

“ማንኛውም በናንተ ላይ ያለው ጸጋ ከአላህ ነው፤ ከዚያም ችግር በደረሰባቸሁ ጊዜ፣ ወደርሱ ብቻ ትጮሃላችሁ።”(ሱረቱ-ነሕል 16፡53)


እዚህም ተመሳሳይ ሀሳብ እናገኛለን፡፡ በኛ ላይ የተዋለው ጸጋ በጠቅላላ ከአላህ ነው ተብሎ እየተነገረን ነው፡፡ ‹ከአላህ› ማለት ግን፡- ከርሱ ዘንድ የተሰጠ፡ አስገኚውና ፈጣሪው እሱ ብቻ የሆነ ማለት እንጂ፡ ከህላዌው የተቆረሰ ማለት አይደለም፡፡

በዛው መልኩ የመርየም ልጅ አል-መሲሕ ዒሳም (ዐለይሂማ-ሰላም) ሕያው የሚሆንበትን ሩሕ (መንፈስ) ለመግለጽ ‹‹ከርሱ የኾነ መንፈስ›› ማለቱ፡- ከአላህ ዘንድ በሆነው ቃል የተገኘና የተፈጠረ ማለት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

4ኛ. ጌታ አላህ አንዳንድ ነገራትን ከመሰሎቻቸው ለይቶ ወደራሱ በማስጠጋት፡- ‹‹ከርሱ የኾነ›› ‹‹የአላህ የኾነ›› በማለት መጥራቱ፡ በዐረብኛው፡- ኢዳፈቱ-ተሸሪፍ ወት-ተክሪም ይባላል፡፡ ማለትም፡- ክብርና ዕልቅናን ለመስጠት ወደ ራስ በማስጠጋት ‹የኔ› የሚል ድምጽ እንዲኖረው ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይህን ሀሳብ የሚደግፉ አንዳንድ ምሣሌዎችን እንመልከት፡-

ሀ/ ባርነት፡- ፍጥረታት በጠቅላላ የአላህ ባሮች ናቸው (መርየም 19፡93)፡፡ ከነዚህ የአላህ ባሮች ውስጥ ጌታ አላህ አማኝ ባሪያዎቹን ለየት በማድረግ፡- ‹ባሮቼን አበስሯቸው› (አዝ-ዙመር 39፡ 17)፣ ‹የአላህ ባሮች ይጠጧታል› (አል-ኢንሳን (አድ-ደህር 76፡ 6)፣ ‹ለባሮቼ ንገሯቸው› (ኢብራሂም 14፡31) ሲል እንሰማለን፡፡ ታዲያ ኹሉም የአላህ ባሪያ ነውና፡ ከሀዲዎችም በዚህ አነጋገር ውስጥ ይካተታሉ ብለን እናምናለንን? በፍጹም አይሆንም፡፡ እዚህ ቦታ ላይ፡ ጌታ አላህ ‹ባሮቼ› ብሎ የሚጠቅሳቸው፡ በፈቃደኝነት እሱን ወደውና ፈርተው ያመለኩትን አማኝ ባሪዎቹን ነው፡፡ እነዚህንም ወደራሱ በማስጠጋት ‹ባሮቼ› ብሎ መጥራቱ፡ ለነሱ ልይዩ ክብርና ማእረግ ነው፡፡

ለ/ መስጂድ፡- መስጂዶች ሁሉ የአላህ ቤቶች ናቸው፡፡ በውስጡ አላህ የሚመለክበት፣ ሥሙ የሚወሳበት፣ ቃሉ የሚነበብበት ስፍራ በመሆኑ፡፡ ታዲያ መስጂዱል ሐረምን (በመካ የሚገኘው ካዕባን) ከሌሎች መሳጂዶች አላህ ለይቶ ‹ቤቴ› ብሎ ጠርቶታል (አል-ሐጅ 22፡26)፡፡ ይህ ማለት ግን ሌሎች መስጂዶች የሱ ቤት ተብለው አይጠሩም ማለት አይደለም፡፡ ባይሆን ትርጉሙ፡- መስጂዱል ሐረም ከሌሎች የአላህ ቤቶች ሁሉ እጅግ የተከበረና የተቀደሰ ስፍራ መሆኑን ነው የሚያመለክተው፡፡ ስለሆነም በውስጡ የሚሰገድ አንድ ሶላት ደረጃው በሌሎች መስጂዶች ከሚሰገድ አንድ ሶላት፡ በአንድ መቶ ሺህ (100.000) እጥፍ እንደሚበልጥ በሐዲሥ ተነገረ፡፡

ሐ/ ግመል፡- ግመሎችና ሌሎች እንሰሳት በጠቅላለ የአላህ ፍጥረት ናቸው (አን-ነሕል 16፡5)፡፡ ሆኖም የነቢዩሏህ ሷሊሕ (ዐለይሂ-ሰላም) ግመልን፡ ከሌሎች ግመሎች ለየት በማድረግ ጌታችን ‹‹የአላህ ግመል›› ብሎ ይጠራታል (አል አዕራፍ 73)፡፡ ምክንያቱም፡- እሷ እንደሌሎቹ ግመሎች በውልደት የተገኘች ሳትሆን፡ ለነቢዩ ሷሊሕ (ዐለይሂ-ሰላም) ተአምርና ማስረጃ ትሆን ዘንድ፡ በአላህ ሁሉን ቻይነት፡ ከቋጥኝ ስር የተገኘች፡ ብቅ ያለች ግመል በመሆኗ ነው፡፡ ሆኖም ግመሎች ሁሉ የአላህ ናቸው፡፡ ፈጣሪያቸው እሱ ነውና፡፡

ወደ መርየም ልጅ ወደ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ስንመለስ ደግሞ፡ ጌታ አላህ እሱን ‹ከርሱ የኾነ መንፈስ› ብሎ ወደራሱ በማስጠጋት የገለጸው፡ በሱ አፈጣጠር ላይ የወንድ (የባል) ጣልቃ ገብነት ሳይኖር፡ መርየም በድንግልናዋ በአላህ ችሎታ የወለደችው በመሆኑ ነው እንጂ፡ ከአላህ የወጣ መንፈስ ሆኖ አይደለም፡፡ አላህ የመንፈስ ፈጣሪና አስገኚ እንጂ እራሱ መንፈስ አይደለም፡፡

5ኛ. ይህንን ሩሕ (መንፈስ) ከጌታ አላህ ተቀብሎ፡ በመርየም ማኅፀን ላይ እፍ ያለባት (የነፋባት) መልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) መሆኑን ከላይ በሱረቱ-መርየም 19፡16-21 ተመልክተናል፡፡ በተጨማሪም ቀጣዮቹን አንቀጾች እንመልከታቸው፡-

“ያችንም ብልቷን የጠበቀቺውን፣ በርሷም ውስጥ ከመንፈሳችን የነፋንባትን እርስዋንም ልጅዋንም (እንደዚሁ)፣ ለዓለማት ታምር ያደረግናትን፣ (መርየምን፣ አታውስ)።”(ሱረቱል አንቢያእ 21፡91)
“የዒምራንን ልጅ መርየምንም ያቺን ብልቷን የጠበቀችውን (ምሳሌ አደረገ)፤ በርሱም ውስጥ ከመንፈሳችን ነፍፋን በጌታዋ ቃላትና በመጽሐፍቱም አረጋገጠች፤ ከታዛዦቹም ነበረች።”(ሱረቱ-ተሕሪም 66፡12)፡፡

በነዚህ ሁለት አንቀጾች ስር ‹‹ነፋፋን እና ነፋንባት›› የሚለውን ቃል በመምዘዝ፡ መልአኩ ጂብሪል ሳይሆን እራሱ አላህ ነው በማኅፀኗ እፍ ያለባት የሚሉ ተከራካሪዎችም ከገጠሟችሁ እንዲህ በማለት ምላሹን ስጧቸው፡-

ሀ/ አላህ የሁሉ ነገር ባለቤትና ፈጣሪ ነው (አል አንዓም 6፡164)፡፡ ትእዛዝም በሰማይም ሆነ በምድር የርሱ ብቻ ነው (አር-ሩም 30፡4)፡፡ ይህ በመሆኑም፡ በቀጥታ በመለኮታዊ ቃሉ እንዲሆን የሻውና ያስገኘው ነገርም ሆነ መላእክትን በማዘዝ በነሱ በኩል የፈጸመውን ነገር ወደራሱ በማስጠጋት ‹‹አደረግነው፣ ፈጸምነው፣ ሰራነው›› በማለት ይገልጻል፡፡ ምክንያቱም እርሱ፡- የበላይ ተቆጣጣሪና አዛዥ፣ ድርጊቱና ስራው እውን እንዲሆን ፈቃጅና ይሁን ባይ ጌታ በመሆኑ ነው፡፡ ከዛ ውጪ አንቀጾቹ በመርየም (ዐለይሃ-ሰላም) ማኅፀን ውስጥ በቀጥታ እፍ ያለባት አላህ እራሱ ነው ማለትን አያስይዙም፡፡ በመልአኩ በኩል የተፈጸሙ ድርጊቶችን አላህ ወደራሱ በማስጠጋት ‹አደረግነው› ብሎ መናገሩ በዒሳ ላይ ብቻ ሳይሆን፡ በሌሎችም ነገራት እንዳለ ለመረዳት፡ ቀጣዮቹን ለአብነት ያህል እንመልከት፡-

1/ ቁርኣን፡- ቅዱስ ቁርኣንን በቃል ደረጃ ከአላህ ተቀብሎ ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ይዞ በመምጣት፡ ለሳቸው ሲያነብላቸው የነበረው መልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) ነው (አል-በቀራህ 2፡97፣ አን-ነሕል 16፡102፣ አሽ-ሹዐራእ 26፡192-194)፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፡ በሌላ አንቀጽ ላይ ደግሞ ጌታ አላህ እንዲህ ይነግረናል፡-

“በርሱ (በቁርአን ንባብ) ልትቸኩል ምላስህን በርሱ አታላውስ። (በልብህ ውስጥ) መሰብሰቡና ማንበቡ (እንድታነበው ማድረግ) በኛ ላይ፣ ነውና። ባነበብነውም ጊዜ (ካለቀ በኋላ) ንባቡን ተከተል። ከዚያም ማብራራቱ በኛ ላይ ነው።”(ሱረቱል ቂያመህ 75፡16-19)

በዚህ አንቀጽ ውስጥ ጌታ አላህ ‹‹ባነበብነውም ጊዜ›› ማለቱን ልብ በሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ግን፡ ጂብሪል እንዲያነብ ባዘዝነውና ባንተም ላይ ባነበበልህ ጊዜ ማለትን ነው፡፡ አላህ ግን ባነበብነውም ጊዜ በማለት ድርጊቱን ወደ ራሱ ማስጠጋቱ የሚያሳየን፡- አላህ የቁርኣኑ ባለቤት፣ የጂብሪል ጌታና ፈጣሪ፣ ወደ ነቢዩ ሙሐመድም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲያነብላቸው የላከው በመኾኑ፡ ሁሉ ነገር በሱ የበላይ ተቆጣጣሪነት ተፈጸመ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ‹‹ባነበብነው ጊዜ›› በማለት ወደ ራሱ በማስጠጋት ተናገረ እንጂ፡ ወደ ምድር በመውረድ ያነበብሁት እኔ ነኝ ማለቱ አይደለም፡፡

ለ/ የበድር ዘመቻ፡- በዚህ ዘመቻ ላይ አስደናቂ ክስተት ተከስቷል፡፡ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወሰላም) እና ሶሓባዎች (ረዲየላሁ ዐንሁም) በሙሽሪኮች ላይ ጭቃን ከመሬት በማንሳት ይወረውሩባቸው ነበር፡፡ ጌታ አላህ ደግሞ የተወረወረው ጭቃ ወደ ሙሽሪኮች አይን እንዲደርስ በኃይሉ ይረዳቸው ነበር፡፡ በዚህ ሰበብም ሙሽሪኮች አስቀያሚ የሆነ ውርደትን ተዋረዱ፡፡ ደግሞም ተገደሉ፡፡ አላህም ክስተቱን እንዲህ ገለጸው፡-

“አልገደልኋቸውም ግን አላህ ገደላቸው፤ (ጭብጥን ዐፈር) በወረወርክም ጊዜ አንተ አልወ ረወርክም፤ ግን አላህ ወረወረ፤ (ወደ ዓይኖቻቸው አደረሰው)፤ ለአማኞችም ከርሱ የሆነን መልካም ጸጋ ለመስጠት (ይህን አደረገ)። አላህ ሰሚ ዐዋቂ ነውና።”(ሱረቱል አንፋል 8፡17-18)

በዚህ አንቀጽ ስር

‹‹በወረወርክም ጊዜ አንተ አልወ ረወርክም፤ ግን አላህ ወረወረ›› የሚል ቃል አልለ፡፡ መጀመሪያ ‹በወረወርክም ጊዜ› በማለት እሳቸው መወርወራቸውን፡ ድርጊቱ በእጃቸው መከናወኑን ያጸድቅና፡ ተመልሶ ደግሞ ‹አንተ አልወረወርክም፤ ግን አላህ ወረወረ› በማለት የሱን ወርዋሪነት ያጸድቃል፡፡ ይህ የሚያሳየን፡- ምንም ከመሬት አንስተህ የወረወርከው አንተ ብትሆንም፡ በሙሽሪኮቹ አይን እንዲደርስ ያደረኩት ግን እኔው አምላክህ አላህ ነኝ የሚል ነው፡፡

ሐ/ አደም (ዐለይሂ-ሰላም)፡- አባታችን አደም የተፈጠረው ከምድር አፈር ነው (አሊ-ዒምራን 3፡59)፡፡ ይህ አፈር ሰው ሆኖ በሕይወት መኖር የጀመረው በውስጡ ሩሕ (መንፈስ) ከተነፋበት በኋላ ነው፡፡ ታዲያ ጌታ አላህ የአደምንም ሩሕ የነፋሁበት እኔው ነኝ እያለን ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን በአደም ሰውነት ውስጥ ሩሕ እንዲገባ የአላህ ፈቃድ መሆኑን ነው እንጂ፡ በቀጥታ የነፋሁበት እኔው ነበርኩ የሚለውን አይደለም፡-

“(ፍጥረቱን) ባስተካከልኩትና በውስጡ ከመንፈሴ በነፋሁበትም ጊዜ ለእርሱ ሰጋጆች ኾናችሁ ውደቁ፡፡”(ሱረቱል ሒጅር 15፡29)

በዛው መልኩ ስለ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ‹‹ከርሱ የኾነ መንፈስ›› በማለት የተነገረውም የሚያስረዳን፡ ከአላህ ዘንድ የተፈጠረና የተገኘ ማለትን እንጂ ሌላን አይደለም፡፡ የሁለ፤ችንም ሩሕ ከአላህ ዘንድ ነውና!! ወላሁ አዕለም፡፡