በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

41፥19 የአላህ ጠላቶች ወደ እሳት የሚሰበሰቡበትን ቀን አስታውስ፡፡ وَيَوْمَ يُحْشَرُ أَعْدَاءُ اللَّهِ إِلَى النَّارِ

"አል ወላእ ወል በራእ" الْوَلَاء وَالْبَرَاء የሚለው የተውሒድ መርሕ "ለአሏህ ብሎ መወደድ እና መጥላት" ቢሆንም በማኅበራዊ እሴት ውስጥ በሚኖረን ጉልኅ ሚና ለሰዎች መልካምን ሥራ እንድንሠራ አምላካችን አሏህ ያዘናል፦

4፥36 አላህንም አምልኩ፡፡ በእርሱም ምንንም አታጋሩ፡፡ ”በወላጆችና በቅርብ ዝምድና ባለቤትም፣ በየቲሞችም፣ በምስኪኖችም፣ በቅርብ ጎረቤትም፣ በሩቅ ጎረቤትም፣ በጎን ባልደረባም፣ በመንገደኛም፣ እጆቻችሁም ንብረት ባደረጓቸው፣ መልካምን ሥሩ”። አላህ ኩራተኛ ጉረኛ የኾነን ሰው አይወድም፡፡ وَاعْبُدُوا اللَّهَ وَلَا تُشْرِكُوا بِهِ شَيْئًا ۖ وَبِالْوَالِدَيْنِ إِحْسَانًا وَبِذِي الْقُرْبَىٰ وَالْيَتَامَىٰ وَالْمَسَاكِينِ وَالْجَارِ ذِي الْقُرْبَىٰ وَالْجَارِ الْجُنُبِ وَالصَّاحِبِ بِالْجَنبِ وَابْنِ السَّبِيلِ وَمَا مَلَكَتْ أَيْمَانُكُمْ ۗ إِنَّ اللَّهَ لَا يُحِبُّ مَن كَانَ مُخْتَالًا فَخُورًا

የወላጆች ሐቅ፣ የዝምድና ሐቅ፣ የጉርብትና ሐቅ መወጣት ግዴታ ነው፥ አንድ አማኝ ለራሱ የሚወደውን ለሌላው እስካልወደደ ድረስ አላመነም፦

ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 1, ሐዲስ 77
አነሥ ኢብኑ ማሊክ”ረ.ዐ.” እንደተረከው፦ ነቢዩም”ﷺ” አሉ፦ ”ከእናንተ አንድም አላመነም ለራሱ የሚወደውን ለወንድሙ እስካልወደደ ድረስ ወይም ለራሱ የሚወደውን ለጎረቤቱ እስካልወደደ ድረስ”፡፡ يُحَدِّثُ عَنْ أَنَسِ بْنِ مَالِكٍ، عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ “‏ لاَ يُؤْمِنُ أَحَدُكُمْ حَتَّى يُحِبَّ لأَخِيهِ – أَوْ قَالَ لِجَارِهِ – مَا يُحِبُّ لِنَفْسِه

ለሰዎች መልካምን መዋል፣ በፍትሕ ማስተካከል፣ ለአሏህ ብሎ ቀጥተኞች በትክክል መስካሪዎች መሆን ሸሪዓችን የሚያዘን ነው፦

60፥8 ከእነዚያ በሃይማኖት ካልተጋደሏችሁ ከአገሮቻችሁም ካላወጡዋችሁ መልካም ብትውሉላቸው እና ወደእነርሱ ብታስተካክሉ አላህ አይከለክላችሁም፡፡ አላህ ትክክለኞችን ይወዳልና፡፡ لَّا يَنْهَاكُمُ اللَّهُ عَنِ الَّذِينَ لَمْ يُقَاتِلُوكُمْ فِي الدِّينِ وَلَمْ يُخْرِجُوكُم مِّن دِيَارِكُمْ أَن تَبَرُّوهُمْ وَتُقْسِطُوا إِلَيْهِمْ ۚ إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ الْمُقْسِطِينَ
5፥8 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለአላህ ቀጥተኞች በትክክል መስካሪዎች ኹኑ፡፡ ሕዝቦችንም መጥላት ባለማስተካከል ላይ አይገፋፋችሁ፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُونُوا قَوَّامِينَ لِلَّهِ شُهَدَاءَ بِالْقِسْطِ ۖ وَلَا يَجْرِمَنَّكُمْ شَنَآنُ قَوْمٍ عَلَىٰ أَلَّا تَعْدِلُوا

ሰውን በቀለሙ፣ በቋንቋው፣ በብሔሩ፣ በዘውጉ መጥላት የፍሕት መጓደል ነው፥ ከዚህ ረገድ አንድ ሙሥሊም ሁሉንም ሰዎች በፍትሕ መያዙ ውዴታን ያሳያል። አንድን ድርጊት ከአድራጊው እንዲሁ አንድን ሥራ ከሠሪው ስለማይነጠል የድርጊቱ እና የሥራው ባለቤት በሚያደርገው ድርጊት እና በሚሠራው ሥራ አሏህ እንደሚወድ እና እንደሚጠላ ሁሉ እኛም አሏህ የደደደውን እንወዳለን የጠላውን እንጠላለን፥ ይህ ፍትሓዊ ብይን ነው። በበጎ ነገር እና አሏህን በመፍራት መረዳዳት የታዘዘ ነው፦

5፥2 በበጎ ነገር እና አላህን በመፍራት ተረዳዱ፡፡ ግን በኃጢአት እና ወሰንን በማለፍ አትረዳዱ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና፡፡ وَتَعَاوَنُوا عَلَى الْبِرِّ وَالتَّقْوَىٰ ۖ وَلَا تَعَاوَنُوا عَلَى الْإِثْمِ وَالْعُدْوَانِ ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ ۖ إِنَّ اللَّهَ شَدِيدُ الْعِقَابِ

ነገር ግን በኃጢአት እና ወሰንን በማለፍ መረዳዳት ክልክል ነው፥ ለምሳሌ፦ በሐራም ሥራ መረዳዳት በኃጢአት መረዳዳት ሲሆን በሺርክ ወይም በኩፍር ሥራ መረዳዳት ወሰንን በማለፍ መረዳዳት ነው።
እዚህ ድረስ ከተግባባ ስለ አል ወላእ ወል በራእ በባይብል እንመልከት! ኢየሱስ፦ "ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ" ብሎ አስተምሯል፦

ዮሐንስ 15፥18 ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። Εἰ ὁ κόσμος ὑμᾶς μισεῖ, γινώσκετε ὅτι ἐμὲ πρῶτον ὑμῶν μεμίσηκεν.

እዚህ አንቀጽ ላይ "ዓለም" ለሚለው የገባው ቃል "ኮስሞስ" κόσμος ሲሆን ሰዎችን ያመለክታል፥ ኢየሱስ ሆነ ሐዋርያትን የጠሉት ሰዎች እንጂ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም አይደለም። ኢየሱስ ሆነ ሐዋርያትን የጠሉት ሰዎች መውደድ ደግሞ ለአምላክ ጥል ነው፥ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የአምላክ ጠላት ሆኖአል፦

ያዕቆብ 4፥4 አመንዝሮች ሆይ! ዓለምን መውደድ ለአምላክ ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የአምላክ ጠላት ሆኖአል። μοιχαλίδες, οὐκ οἴδατε ὅτι ἡ φιλία τοῦ κόσμου ἔχθρα τοῦ Θεοῦ ἐστιν; ὃς ἐὰν οὖν βουληθῇ φίλος εἶναι τοῦ κόσμου, ἐχθρὸς τοῦ Θεοῦ καθίσταται.

"ሰዎች እንዴት የአሏህ ጠላቶች ይሆናሉ? አሏህ እንዴት ሰዎችን ይጠላል" ብላችሁ ለጠየቃችሁ እንኳን ያሻረከ እና የከፈረ ይቅርና የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የአምላክ ጠላት ነው፥ አስማተኛ፣ መተተኛ፣ በድግምት የሚጠነቍል ድግምተኛ፣ መናፍስትን የሚጠራ፣ ጠንቋይም፣ ሙታን ሳቢም በአምላክ ፊት የተጠላ ነው፦

ዘዳግም 18፥11-12 አስማተኛም፥ መተተኛም፥ በድግምት የሚጠነቍልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቋይም፥ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በያህዌህ ፊት "የተጠላ" ነው።

በባይብል ፈጣሪ ኃጢአተኞችን ከመጥላትም ባሻገር በገሃነም ይቀጣ የለ? አንድ ሰው የፈጣሪን መልእክተኛ ለመከተል ሲመጣ ቤተሰቡ እና የራሱን ሕይወት ሊጠላ ይገባዋል፦

ሉቃስ 14፥26 ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱን እና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።

"መጥላት" ማለት "ከራሱ እና ከቤተሰቡ ይልቅ አስበልጦ መውደድ" ማለት ከሆነ እኛም ሙሥሊሞችም ለዲናችን ብለን የማያምኑትን እንጠላለን ማለት ከማያምኑት ይልቅ አስበልጠን ሙሥሊም ወንድማችንን እና እኅታችንን እንወዳለን ማለት ነው። ሰዎች ከአሏህ ሌላ ባለንጣዎችን አሏህን እንደሚወዱ ሊወዱ ቢችሉም አማኞች ግን አሏህን በመውደድ ከከሓድያን የበረቱ ናቸው፦


2፥165 ከሰዎችም ከአላህ ሌላ ባለንጣዎችን አላህን እንደሚወዱ የሚወዷቸው ኾነው የሚይዙ አሉ፡፡ እነዚያ ያመኑትም አላህን በመውደድ ከእነርሱ ይበልጥ የበረቱ ናቸው፡፡ وَمِنَ النَّاسِ مَن يَتَّخِذُ مِن دُونِ اللَّهِ أَندَادًا يُحِبُّونَهُمْ كَحُبِّ اللَّهِ ۖ وَالَّذِينَ آمَنُوا أَشَدُّ حُبًّا لِّلَّهِ ۗ

አሏህ ሂያዳህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ

ወሠላሙ ዐለይኩም