በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
2፥117 ነገርን ማስገኘት በሻ ጊዜ ለእርሱ የሚለው «ኹን» ነው ወዲያውም ይኾናል፡፡ وَإِذَا قَضَىٰ أَمْرًا فَإِنَّمَا يَقُولُ لَهُ كُن فَيَكُونُ
"ዑሉው" عُلُوّ የሚለው ቃል "ዐላ" عَلَا ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ሉዓላዊነት" ማለት ነው፥ አምላካችን አሏህ ከሁሉ በላይ "ልዑል" ስለሆነ "አል-ዓሊይ" العَلِيّ ነው፦
2፥255 እርሱም የሁሉ በላይ ታላቅ ነው፡፡ وَهُوَ الْعَلِيُّ الْعَظِيمُ
እዚህ አንቀጽ ላይ "የሁሉ በላይ" ለሚለው የገባው ቃል "አል-ዓሊይ" العَلِيّ ሲሆን "የበላይ" "ምጡቅ" "ልዑል" ማለት ነው፥ "ልዑል" የሚለው የግዕዝ ቃል እራሱ "የሁሉ በላይ" ማለት ነው። "ልዕልና" ወይም "ሉዓላዊነት" ማለት "የበላይነት" "ምጥቀት" ማለት ነው፥ በጥቅሉ "ዑሉዉል ሏህ" عُلُوّ اللَّه ማለት "የአሏህ ሉዓላዊነት"sovereignty of Allah" ማለት ነው። የአሏህ ሉዓላዊነት ሙጅመል ነው፥ "ሙጅመል" مُجّمَل ማለት "ጥቅል"general" ማለት ነው፥ አምላካችን አሏህ በጥቅሉ ፍጥረትን እርሱ ሽቶ እና ፈቅዶ ኹን በሚል ቃሉ ወስኖ ማስገኘቱ የአሏህ ሉዓላዊነት ነው፦
2፥117 ነገርን ማስገኘት በሻ ጊዜ ለእርሱ የሚለው «ኹን» ነው ወዲያውም ይኾናል፡፡ وَإِذَا قَضَىٰ أَمْرًا فَإِنَّمَا يَقُولُ لَهُ كُن فَيَكُونُ
3፥47 ነገርን ማስገኘት በሻ ጊዜ ለእርሱ የሚለው «ኹን» ነው ወዲያውም ይኾናል፡፡ إِذَا قَضَىٰ أَمْرًا فَإِنَّمَا يَقُولُ لَهُ كُن فَيَكُونُ
19፥35 ነገርን ማስገኘት በሻ ጊዜ ለእርሱ የሚለው «ኹን» ነው ወዲያውም ይኾናል፡፡ إِذَا قَضَىٰ أَمْرًا فَإِنَّمَا يَقُولُ لَهُ كُن فَيَكُونُ
40፥68 ነገርን ማስገኘት በሻ ጊዜ ለእርሱ የሚለው «ኹን» ነው ወዲያውም ይኾናል፡፡ فَإِذَا قَضَىٰ أَمْرًا فَإِنَّمَا يَقُولُ لَهُ كُن فَيَكُونُ
እነዚህ አናቅጽ ላይ "በሻ" ለሚለው የገባው ቃል "ቀዷ" قَضَىٰ ሲሆን "አራደ" أَرَادَ ማለት ነው፥ "አራደ" أَرَادَ ማለት "ፈለገ" "ፈቀደ" "አሻ" ማለት ነው፦
36፥82 ነገሩም አንዳችን ማስገኘት በሻ ጊዜ ኹን ማለት ነው፡፡ ወዲያው ይኾናልም፡፡ إِنَّمَا أَمْرُهُ إِذَا أَرَادَ شَيْئًا أَن يَقُولَ لَهُ كُن فَيَكُونُ
እዚህ አንቀጽ ላይ "በሻ" ለሚለው የገባው ቃል "አራደ" أَرَادَ ሲሆን በመጀመሪያ መደብ "አረድና" أَرَدْنَا በማለት ተናግራል፦
16፥40 ለማንኛውም ነገር መኾኑን "በሻነው" ጊዜ ቃላችን ለእርሱ “ኹን” ማለት ብቻ ነው፥ ወዲውም ይኾናል፡፡ إِنَّمَا قَوْلُنَا لِشَيْءٍ إِذَا أَرَدْنَاهُ أَن نَّقُولَ لَهُ كُن فَيَكُونُ
"አረድና-ሁ" أَرَدْنَاهُ ማለት "በወሰነው" "በፈለግነው" "በፈቀድነው" በሻነው" ማለት ነው፥ አምላካችን አሏህ ሽቶ እና ፈቅዶ ኹን በሚል ቃሉ ወስኖ ማስገኘቱ ጥቅላዊ የአሏህ ሉዓላዊነት ነው፦
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 40, ሐዲስ 19
አቡ ሁረይራህ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛ”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ "አሏህ ፍጥረትን ባሻ ጊዜ እራሱ በመጽሐፉ ጻፈ። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم " لَمَّا قَضَى اللَّهُ الْخَلْقَ كَتَبَ فِي كِتَابِهِ عَلَى نَفْسِهِ
እነዚህ ሐዲስ ላይ "በሻ" ለሚለው የገባው ቃል "ቀዷ" قَضَىٰ ሲሆን ፍጥረትን ከመፍጠሩ በፊት የፍጥረትን ሂደት ቀድሞ ስለሚያውቀው ጽፎታል።
አሏህ ለሰው ልጅ ውሥዕ፣ ተክሊፍ፣ መሺዓህ፣ ኢጥላቅ ሰቶ በሰጣቸው ጸጋ መጠየቁ፣ መሸለሙ እና መቅጣቱ ሙፈሰል ነው፥ "ሙፈሰል" مُفَصَّل ማለት "ተናጥል"particular" ማለት ነው። “መሥኡሉል አደብ” مَسْؤُول الاَدَب ማለት “ግብረገባዊ ተጠያቂነት”moral accountability” ማለት ነው፥ “ተክሊፍ” تَكْلِيف የሚለው ቃል “ከለፈ” كَلَّفَ ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን የተጣለብን "ድርሻ" "ግዴታ" "አላፍትና" ማለት ነው። አሏህ በሠራው እና በሚሠራው ሥራ አይጠየቅም፥ ሰው ግን በተሰጠው ጸጋ ለሚሠራው ሥራ ይጠየቃል፦
21፥23 ከሚሠራው ሁሉ አይጠየቅም፡፡ እነርሱ ግን ይጠየቃሉ፡፡ لَا يُسْأَلُ عَمَّا يَفْعَلُ وَهُمْ يُسْأَلُونَ
16፥93 ትሠሩት ከነበራችሁትም ሁሉ በእርግጥ ትጠየቃላችሁ፡፡ وَلَتُسْأَلُنَّ عَمَّا كُنتُمْ تَعْمَلُون
102፥8 ከዚያም ከጸጋችሁ ሁሉ በዚያ ቀን ትጠየቃላችሁ። ثُمَّ لَتُسْأَلُنَّ يَوْمَئِذٍ عَنِ النَّعِيمِ
“ነዒም” نَّعِيم ማለት “ጸጋ” ማለት ሲሆን ይህ የተሰጠን ጸጋ አድርግ የተባለውን የመታዘዝና ያለመታዘዝ እንዲሁ አታድርግ የተባለውን የመከልከልና ያለመከልከል ነጻ ፈቃድ ነው፥ “መሺዓህ” مَشِئَة ማለት “ነጻ ፈቃድ”free will” ማለት ነው፦
18፥29 «እውነቱም ከጌታችሁ ነው፡፡ የፈቀደ ሰው ይመን፤ የፈቀደ ሰው ይካድ» በላቸው፡፡ وَقُلِ الْحَقُّ مِن رَّبِّكُمْ ۖ فَمَن شَاءَ فَلْيُؤْمِن وَمَن شَاءَ فَلْيَكْفُر
“ፈቀደ” ለሚለው የግሥ መደብ የገባው ቃል “ሻአ” شَاءَ ሲሆን "ኢጥላቅ" إِطْلَاق ማለትም "ነጻነት"libration" ነው፥ ይህ ምርጫ ከአሏህ ዘንድ ዋጋ የሚያስከፍል ዛቻ ነው። ሰዎች በተሰጣቸው ነጻ ፈቃድ ይሠሩት የነበሩትን መልካም ነገር ይመነዳሉ፥ በተቃራኒው ይሠሩት የነበሩትን መጥፎ ነገር ይቀጣሉ፦
18፥180 “ይሠሩት የነበሩትን ነገር በእርግጥ ይመነዳሉ”፡፡ سَيُجْزَوْنَ مَا كَانُوا يَعْمَلُونَ
6፥120 “እነዚያ ኃጢአትን የሚሠሩ ይሠሩት በነበሩት ነገር በእርግጥ ይቀጣሉ”፡፡ نَّ الَّذِينَ يَكْسِبُونَ الْإِثْمَ سَيُجْزَوْنَ بِمَا كَانُوا يَقْتَرِفُونَ
ስለዚህ ሰው ሲፈጠር በነጻ ፈቃዱ መታዘዝ እና ማመጽ የሚችልበትን ችሎታ ተሰቶት ነው፦
23፥62 ማንኛይቱንም ነፍስ ችሎታዋን እንጂ አናስገድዳትም፡፡ وَلَا نُكَلِّفُ نَفْسًا إِلَّا وُسْعَهَا
“ውሥዕ” وُسْع ማለት “ችሎታ” ማለት ሲሆን ሰው አሏህ “አድርግ” ብሎ ያዘዘውን የማድረግ እና “አታድርግ” ብሎ የከለከውን ያለማድረግ ችሎታ እና ዐቅም ያሳያል። አምላካችን አሏህ፦ “በጎ ሥራን ሥሩ” እና “ወሰንንም አትለፉ” ማለቱ በራሱ ሰው በጎ ሥራን የመሥራት እና ያለመሥራት ወይም ወሰን ማለፍ እና አለማለፍ ዐቅም እንዳለው የሚያሳይ ነው፦
2፥195 በጎ ሥራን ሥሩ! አላህ በጎ ሠሪዎችን ይወዳልና፡፡ وَأَحْسِنُوا ۛ إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ الْمُحْسِنِينَ
5፥87 ወሰንንም አትለፉ፡፡ አላህ ወሰን አላፊዎችን አይወድምና፡፡ وَلَا تَعْتَدُوا ۚ إِنَّ اللَّهَ لَا يُحِبُّ الْمُعْتَدِينَ
ሰው ነጻ ፈቃድ ባይኖረው ኖሮ መሥራት እና አለመሥራት ዐቅም እና ችሎታ የሌለውን ነገር “ሥራ” እና “አትሥራ” የሚል ሙሐከማት መስጠቱ ትርጉም አይኖረውም ነበር፥ አሏህ በጎ ሠሪዎችን የሚወደው በሚሠሩት በጎ ሥራ ሲሆን እና ወሰን አላፊዎችን የሚጠላው ደግሞ በሚሠሩት መጥፎ ሥራ ነው። ሰው በተሰጠው የማድረግ እና ያለማድረግ ነጻ ፈቃድ በዱንያህ ይፈተናል፦
6፥165 እርሱም ያ በምድር ምትኮች ያደረጋችሁ "በሰጣችሁም ጸጋ ሊፈትናችሁ" ከፊላችሁን ከከፊሉ በላይ በደረጃዎች ከፍ ያደረገ ነው፡፡ وَهُوَ الَّذِي جَعَلَكُمْ خَلَائِفَ الْأَرْضِ وَرَفَعَ بَعْضَكُمْ فَوْقَ بَعْضٍ دَرَجَاتٍ لِّيَبْلُوَكُمْ فِي مَا آتَاكُمْ ۗ إِنَّ رَبَّكَ سَرِيعُ الْعِقَابِ وَإِنَّهُ لَغَفُورٌ رَّحِيمٌ
የተሰጠን ጸጋ አድርግ የተባለውን የመታዘዝና ያለመታዘዝ፥ አታድርግ የተባለውን የመከልከልና ያለመከልከል ፈተና ስለሆነ “በሰጣችሁም ጸጋ ሊፈትናችሁ” ይለናል፥ “ሐዘር” حَذَر ማለት “ጥንቃቄ”discretion” ማለት ሲሆን አምላካችን አሏህ፦ "ጥንቃቄአችሁን ያዙ" "እራሳችሁን ከእሳት ጠብቁ" የሚለው ማስጠንቀቂ ትርጉም ያለው ሰው ግብረገባዊ ተጠያቂነት ስላለው ነው፦
4፥71 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ጥንቃቄአችሁን ያዙ፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا خُذُوا حِذْرَكُمْ
5፥105 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እራሳችሁን ከእሳት ጠብቁ፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا عَلَيْكُمْ أَنفُسَكُمْ
66፥6 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እራሳችሁን እና ቤተሰቦቻችሁን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ደንጋዮች ከኾነች እሳት ጠብቁ፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا قُوا أَنفُسَكُمْ وَأَهْلِيكُمْ نَارًا وَقُودُهَا النَّاسُ
አምላካችን አሏህ ፍትሓዊ አምላክ ሰለሆነ ማንንም አይበድልም፥ “ዘራህ” ذَرَّة ማለት “ቅንጣት”atom” ማለት ሲሆን አሏህ ቅንጣት ታክል ማንንም አይበድልም። ነገር ግን ሰው እራሱን የሚበድነው ማመን እና መታዘዝ ሲችል በመካድ እና በማመጽ ነው፦
18፥49 ጌታህም አንድንም አይበድልም፡፡ وَلَا يَظْلِمُ رَبُّكَ أَحَدًا
4፥40 አላህ የብናኝን ክብደት ያህል አይበድልም፡፡ إِنَّ اللَّهَ لَا يَظْلِمُ مِثْقَالَ ذَرَّةٍ
10፥44 አላህ ሰዎችን ምንም አይበድልም፡፡ ግን ሰዎች እራሳቸውን ይበድላሉ፡፡ إِنَّ اللَّهَ لَا يَظْلِمُ النَّاسَ شَيْئًا وَلَـٰكِنَّ النَّاسَ أَنفُسَهُمْ يَظْلِمُونَ
የአሏህ ሉዓላዊነት እና የሰው ነጻ ፈቃድ በፍጹም የሚጋጩ ነገሮች አይደሉም፥ የአሏህ ሉዓላዊነት ጥቅላዊ ነገር ሲሆን የሰው ፈቃድ ደግሞ በአሏህ ሉዓላዊነት ሥር ያለ ተናጥሏዊ ነገር ነው። አሏህ የእርሱ ዑሉው ተረድተን የተሰጠንን ጸጋ ባግባብ የምንጠቀም ያርገን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
ወሠላሙ ዐለይኩም
ቀደር