በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

18፥49 ጌታህም አንድንም አይበድልም፡፡ وَلَا يَظْلِمُ رَبُّكَ أَحَدًا

አምላካችን አሏህ ፍትሓዊ አምላክ ሰለሆነ ማንንም አይበድልም፥ “ዘራህ” ذَرَّة ማለት “ቅንጣት”atom” ማለት ሲሆን አሏህ ቅንጣት ታክል ማንንም አይበድልም። ነገር ግን ሰው እራሱን የሚበድነው ማመን እና መታዘዝ ሲችል በመካድ እና በማመጽ ነው፦

18፥49 ጌታህም አንድንም አይበድልም፡፡ وَلَا يَظْلِمُ رَبُّكَ أَحَدًا
4፥40 አላህ የብናኝን ክብደት ያህል አይበድልም፡፡ إِنَّ اللَّهَ لَا يَظْلِمُ مِثْقَالَ ذَرَّةٍ
10፥44 አላህ ሰዎችን ምንም አይበድልም፡፡ ግን ሰዎች እራሳቸውን ይበድላሉ፡፡ إِنَّ اللَّهَ لَا يَظْلِمُ النَّاسَ شَيْئًا وَلَـٰكِنَّ النَّاسَ أَنفُسَهُمْ يَظْلِمُونَ

ባለማወቅ የሚሠራ መጥፎ ሥራ “ስህተት” ሲባል በመርሳት የማይሠራ መልካም ሥራ “ግድፈት” ይባላል፥ አሏህ ሰዎች ባለማወቅ በሠሩት ስህተት ሆነ በመርሳት በማይሠሩት ግድፈት አይቀጣም፦

2፥286 “ጌታችን ሆይ! ”ብንረሳ ወይም ብንስት አትቅጣን” በሉ፡፡ رَبَّنَا لَا تُؤَاخِذْنَا إِن نَّسِينَا أَوْ أَخْطَأْنَ
33፥5 በእርሱ በተሳሳታችሁበትም ነገርም በእናንተ ላይ ኃጢአት የለባችሁም፥ ግን ልቦቻችሁ ዐዉቀው በሠሩት ኃጢአት አለባችሁ”። አላህም መሃሪ አዛኝ ነው። وَلَيْسَ عَلَيْكُمْ جُنَاحٌۭ فِيمَآ أَخْطَأْتُم بِهِۦ وَلَٰكِن مَّا تَعَمَّدَتْ قُلُوبُكُمْ ۚ وَكَانَ ٱللَّهُ غَفُورًۭا رَّحِيمًا

“ብንረሳ” ማለት መሥራቱ ግዴታ የሆነ መልካም ሥራ በመርሳት መግደፍ ሲሆን “ብንስት” ማለት መሥራቱ ክልክል የሆነ መጥፎ ሥራ ባለማወቅ መሳሳት ነው። በተሳሳትንበት ነገር በእኛ ላይ ኃጢአት የለብንም፥ ቅሉ ግን ልባችን እያወቀው በሠራነው መጥፎ ሥራ ኃጢአት አለበት። ሰው ድርሻው በሌለበት እና ጣልቃ ገብ ባልሆነበት ጉዳይ ተገዶ ነውና የተገደዱበት ነገር አያስጠይቅም አያስቀጣም፦

2፥173 ሽፍታ እና ወሰን አላፊ ሳይኾን ለመብላት "የተገደደ ሰውም በእርሱ ላይ ኃጢኣት የለበትም"፥ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡ فَمَنِ اضْطُرَّ غَيْرَ بَاغٍ وَلَا عَادٍ فَلَا إِثْمَ عَلَيْهِ ۚ إِنَّ اللَّهَ غَفُورٌ رَّحِيمٌ
ሡነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 10, ሐዲስ 2123
ኢብኑ ዐባሥ እንደተረከው፦ “ነቢዩም”ﷺ” አሉ፦ ”አላህ በኡማዬ ላይ ስህተት፣ መርሳት እና የገተደዱበትን ነገር አንስቷል”። عَنِ ابْنِ عَبَّاسٍ، عَنِ النَّبِيِّ ـ صلى الله عليه وسلم ـ قَالَ ‏ “‏ إِنَّ اللَّهَ وَضَعَ عَنْ أُمَّتِي الْخَطَأَ وَالنِّسْيَانَ وَمَا اسْتُكْرِهُوا عَلَيْهِ

“ውሥዕ” وُسْع ማለት “ችሎታ” ማለት ሲሆን ሰው አሏህ “አድርግ” ብሎ ያዘዘውን የማድረግ እና “አታድርግ” ብሎ የከለከውን ያለማድረግ ችሎታ እና ዐቅም ያሳያል፥ ጌታችን አሏህ ፍትሓዊ ስለሆነ ማንኛይቱንም ነፍስ ችሎታዋን እንጂ አያስገድድም፦

23፥62 ማንኛይቱንም ነፍስ ችሎታዋን እንጂ አናስገድዳትም፡፡ وَلَا نُكَلِّفُ نَفْسًا إِلَّا وُسْعَهَا

“ኪራመን ካቲቢን” كِرَامًا كَاتِبِين ማለት “የተከበሩ ጸሐፊዎች” ማለት ሲሆን እነዚህ ጸሐፊዎች በእያንዳንዱ ሰው ቀኝ እና ግራ ያሉ ሁለት መላእክት ናቸው፥ በቀኝ ያለው መልአክ ሠናይ ተግባራትን በብዕር ሲመዘግብ በግራ ያለው መልአክ ደግሞ እኩይ ተግባራትን በብዕር ይመዘግባል። እነዚህ መላእክት በእንቅልፍ ልብ፣ በዕብደት እና በእንጭጭነት የሚደረግ ሥራ አይመዘግቡትም፦

68፥1 “ኑን”፤ በብርዕ እምላለሁ፥ በዚያም በሚጽፉት”። نٓ ۚ وَٱلْقَلَمِ وَمَا يَسْطُرُونَ
ሡነን አቢ ዳውድ መጽሐፍ 40, ሐዲስ 48
ዓኢሻህ "ረ.ዐ." እንደተረከው፦ "የአላህ መልእክተኛ”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ "ብዕር ከሦስት ሰዎች ተነስቷል። እነርሱም፦ የተኛ ሰው እስኪነሳ ድረስ፣ ዕብደ ወደ ዐቅሉ እስኪመለስ ድረስ፣ ልጅ እስኪጎሎብት ድረስ"። عَنْ عَائِشَةَ، رضى الله عنها أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ "‏ رُفِعَ الْقَلَمُ عَنْ ثَلاَثَةٍ عَنِ النَّائِمِ حَتَّى يَسْتَيْقِظَ وَعَنِ الْمُبْتَلَى حَتَّى يَبْرَأَ وَعَنِ الصَّبِيِّ حَتَّى يَكْبَرَ ‏

ይህ የአሏህ ፍትሓዊነት ምን ያህል ጥልቅ እና ምጥቅ መሆኑን የሚያሳይ ነው፥ የተመራ ሰው የሚመራው ለራሱ ብቻ ነው። የጠመመም ሰው የሚሚጠመው ጉዳቱ በእርሷ ላይ ነው፥ ተሸካሚም ነፍስ የሌላይቱን ነፍስ ኃጢኣት አትሸከምም፡፡ እንደውም አንድ የአሏህ መልእክተኛ ይዞት የመጣውን መልእክት ያልሰማ አይቀጣም፦

17፥15 የተመራ ሰው የሚመራው ለራሱ ብቻ ነው፥ የጠመመም ሰው የሚሚጠመው ጉዳቱ በእርሷ ላይ ነው፡፡ ተሸካሚም ነፍስ የሌላይቱን ነፍስ ኃጢኣት አትሸከምም፡፡ መልእክተኛንም እስከምንልክ ድረስ የምንቀጣ አይደለንም፡፡ مَّنِ اهْتَدَىٰ فَإِنَّمَا يَهْتَدِي لِنَفْسِهِ ۖ وَمَن ضَلَّ فَإِنَّمَا يَضِلُّ عَلَيْهَا ۚ وَلَا تَزِرُ وَازِرَةٌ وِزْرَ أُخْرَىٰ ۗ وَمَا كُنَّا مُعَذِّبِينَ حَتَّىٰ نَبْعَثَ رَسُولًا

"መልእክተኛንም እስከምንልክ ድረስ የምንቀጣ አይደለንም" የሚለው ይሰመርበት! "ፈህም" فَهْم የሚለው ቃል "ፈሂመ" فَهِمَ ማለትም "ተረዳ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "መረዳት"understanding" ማለት ነው፥ "መዕና" مَعْنًى የሚለው ቃል "ዐነ" عَنَى ማለትም "ተረጎመ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ትርጉም"meaning" ማለት ነው። አንድ ሰው መልእክተኛ ይዞት የመጣውን መልእክት አመመስማት ብቻ ሳይሆን የመልእክቱን ፈህም እና መዕና ካላወቀ አይቀጣም፥ ይህ "ዑዝር ቢል-ጀህል" عُذْر بِالجَهْل ነውና።
"ኒያህ" نِيَّة የሚለው ቃል "ነዋ" نَوَى ማለትም "ወጠነ" ከሚለው ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ውጥን"intention" ማለት ነው። ሥራ የሚለካው በኒያህ ነው፥ ማንኛውምንም ሰው የነየተውን ያገኛል። የፍርዱ ቀን ሰዎች ተቀስቅሰው ምንዳ እና ፍዳ የሚበየንባቸው በነየቱት ኒያህ ነው፦

ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 2, ሐዲስ 47
ዑመር እንደተረከው፦ "የአሏህ መልክተኛ"ﷺ" እንዲህ ብለዋል፦ "ሥራ የሚለካው በኒያህ ነው፥ ማንኛውምንም ሰው የነየተውን ያገኛል። عَنْ عُمَرَ، أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ “‏ الأَعْمَالُ بِالنِّيَّةِ، وَلِكُلِّ امْرِئٍ مَا نَوَى
ሡነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 37, ሐዲስ 4370
አቢ ሁራይራህ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛ"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "ሰዎች ተቀስቅሰው የሚበየንባቸው በነየቱት ነው"። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ ـ صلى الله عليه وسلم ـ ‏:‏ ‏ “‏ إِنَّمَا يُبْعَثُ النَّاسُ عَلَى نِيَّاتِهِمْ

ሰዎች የምንፈርደው በምላስ በተነገረን እና በውጫዊ አካል በሚደረገው ድርጊት እንጂ በልብ ላይ በተቀመጠው ኒያህ አይደለም፥ በፍርዱ ቀን በሁሉም ላይ በእውነት እና በትክክሉ ፈራጁ አሏህ ነው፦

34፥26 «ጌታችን በመካከላችን ይሰበስባል፡፡ ከዚያም በመካከላችን በእውነት ይፈርዳል፡፡ እርሱም በትክክል ፈራጁ ዐዋቂው ነው» በላቸው፡፡ قُلْ يَجْمَعُ بَيْنَنَا رَبُّنَا ثُمَّ يَفْتَحُ بَيْنَنَا بِالْحَقِّ وَهُوَ الْفَتَّاحُ الْعَلِيمُ

አምላካችን አሏህ የእርሱን ፍትሕ ከሚያስተነትኑት ያድርገን! አሚን።

✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ

ወሠላሙ ዐለይኩም
ነገረ ድኅነት