በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
4፥171 «ሦስት ነው» አትበሉ! ተከልከሉ! ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና፡፡ አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ وَلَا تَقُولُوا ثَلَاثَةٌ ۚ انتَهُوا خَيْرًا لَّكُمْ ۚ إِنَّمَا اللَّهُ إِلَـٰهٌ وَاحِدٌ
"መለኮት" ማለት "አምላክነት" ማለት ነው፥ "እግዚአብሔር" የሚለው ቃል ደግሞ በግሪክ "ቴዎስ" θεός ሲሆን "አምላክ"God" ማለት ነው። በጥቅሉ "መለኮት" "እግዚአብሔር" "አምላክ" ተመሳሳይ ነገር ለማሳየት የመጣ ሲሆን በሥላሴ እሳቤ፦
1.ወላዲ ማንነት አምላክ፣
2. ተወላዲ ማንነት አምላክ፣
3. ሰራጺ ማንነት አምላክ
ከሆነ ወላዲ አምላክ፣ ተወላዲ አምላክ፣ ሰራጺ አምላክ አለ ማለት ነው፦
ሰይፈ ሥላሴ ዘሰኞ ምዕራፍ 2 ቁጥር 42
"በጽርሐ አርያም ለሚኖር ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል"
"ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ" የሚለው ይሰመርበት! "ሦስት ለሚሆን አምላክ" በግዕዙ "ሥሉስ አምላክ" ነው። ወላዲ አምላክ "አብ" ተወላዲ አምላክ እና ሰራጺ አምላክ ካልሆነ፣ ተወላዲ አምላክ "ወልድ" ወላዲ አምላክ እና ሰራጺ አምላክ ካልሆነ፣ ሰራጺ አምላክ "መንፈስ ቅዱስ" ወላዲ አምላክ እና ተወላዲ አምላክ ካልሆነ ስንት አምላክ አለ? መልሱ ሦስት አምላክ ይሆናል። ምክንያቱም ወላዲ አምላክ፣ ተወላዲ አምላክ፣ ሰራጺ አምላክ ሦስት ነው፥ እነርሱም፦ በግዕዙ "ሦሉስ አምላክ" ሲሉ ትርጉሙ "ሦስት አምላክ" ማለት ነው፦
ሰይፈ ሥላሴ ዘረቡዕ ምዕራፍ 4 ቁጥር 31
“መለኮት በአካል ሦስት ሲሆን በባሕርይ አንድ ነው”።
"መለኮት በአካል ሦስት ሲሆን" የሚለው ይሰመርበት! "መለኮት በአካል ሦስት ነው" ማለት የጤንነት ነውን? አምላክ አባት(እግዚአብሔር አብ)፣ አምላክ ልጅ(እግዚአብሔር ወልድ)፣ አምላክ መንፈስ ቅዱስ(እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ) የሚባሉ በአካል ሦስት አምላክ"tritheism" ናቸው። አምላክነት ሦስቱ አካላት የሚጋሩት ባሕርይ እንጂ "ማንነት ነው" ብለው አያምኑም፦
ሰይፈ ሥላሴ ዘሐሙስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 17
"ሦስት የእሳት ባሕርይ ነገር ግን አንድ ብርሃን ነው"።
"ሦስት የእሳት ባሕርይ" የሚለው ይሰመርበት! "ሦስት የእሳት ባሕርይ" ካለ አንድ ብርሃን ሳይሆን ሦስት ብርሃናት ናቸው፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 10 ቁጥር 6
"ዕውቀትን የሚገልጹ ብርሃናት ናቸው"።
"ብርሃናት" የብርሃን ብዙ ቁጥር ነው፥ አንዱ ብርሃን አብ ሁለቱ ብርሃናትን ወልድ እና መንፈስ ቅዱስን አስገኘ ማለት የጤንነት አይደለም፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 10 ቁጥር 12
"አብ ብርሃን ነው፣ ከአብ የተወለደ ቃሉ ወልድ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ነው፣ እንዲሁ ከአብ የሠረፀ መንፈስ ቅዱስም ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ነው"።
ከአንዱ ብርሃን ከአብ ወልድ የሚባል ብርሃን በመወለድ ተገኘ እና ከአንዱ ብርሃን ከአብ መንፈስ ቅዱስ የሚባል ብርሃን በመሥረፅ ተገኘ የሚል ትምህርት በግልጽ "ሦስት ፀሐይ" ብለው አስቀምጠዋል፦
ሰይፈ ሥላሴ ዘረቡዕ ምዕራፍ 4 ቁጥር 21
"ሦስት ፀሐይ አንድ ብርሃን.. ነው"።
ሰይፈ ሥላሴ ዘሐሙስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 21
"ሦስት የብርሃን አዕማድ በመጠን ግን..አንድ ነው"።
ዶክተር ዛኪር፣ ዶክተር ቢላል እና ዶክተር ፊሊፕ ሦስት ዶክተር እንጂ አንድ ዶክተር አይደሉም፥ ግን አንድ ዶክትሬት ይጋራሉ። በተመሳዳይ እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ እና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሦስት እግዚአብሔር እንጂ አንድ እግዚአብሔር አይደሉም፥ ግን አንድ እግዚአብሔርነትን ይጋራሉ፦
ሰይፈ ሥላሴ ዘማክሰኞ ምዕራፍ 3 ቁጥር 21
"ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ሦስት ሲሆን አንድ፥ አንድ ሲሆን ሦስት የሚሆን እርሱ አንድ ቅዱስ ነው"።
"እግዚአብሔር ሦስት ሲሆን" የሚለው ይሰመርበት! "አንድ ቅዱስ ነው" ካላችሁ በኃላ "ሥሉስ ቅዱስ" ማለትም "ሦስት ቅዱስ" ማለታችሁ የጤና ነውን? "ቅድስት ሥላሴ" ማለትም "ቅዱሶች ሦስነት" ለምን ትላላችሁ? በነገራችን ላይ "ቅድስት" የሚለው ቃል "ቅዱሳን" "ቅዱሶች" የሚለውን ለመተካት የሚጠቀሙበት ነው፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 82 ቁጥር 14
"ሥሉስ ቅዱስ ያልተፈጠሩ ናቸው"
"ሦስት ቅዱስ" "አንድ ቅዱስ" እርስ በእርሱ ይጋጫል። እንደ እናንተ ትምህርት አምላክ ከማርያም ሲወለድ የተወለደው አንዱ አምላክ ነው ወይስ ሁለተኛው ልጅ የሆነ አምላክ? አንዱ አምላክ ከሆነ አብ እና መንፈስ ቅዱስ አብረው ተወልደዋል? ምክንያቱም ማርያም የመለኮት እናት ናት ስለሚል፦
ሰይፈ ሥላሴ ዘእሑድ ምዕራፍ 8 ቁጥር 73
"በመለኮት እናት በድንግል ማርያም"።
ሁለተኛው ልጅ የሆነው አምላክ ከሆነ ያልተወለዱ ሁለት አባት እና መንፈስ ቅዱስ የሆኑ አምላክ አሉን? ከማርያም የተነሳው ሥጋ መለኮትን ገንዘብ ሲያደርግ ሙሉ መለኮትን ነው ወይስ የአብ ተወላዲ መለኮትን?
ያለው አማራጭ ሦስት አምላክ ስለሆነ በግልጽ "አምላካችን ያለ መለየት ሦስት ነው" ብለው አርፈውታል፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 99 ቁጥር 11
“አምላካችን ያለ መለየት ሦስት ነው”።
"ኡሲያ" οὐσία የሚለው ቃል "ሃልዎት" "ኑባሬ" "ህላዌ"essence" የሚል ትርጉም አለው፥ "በአካል ሦስት ህላዌ" ማለት የጤንነት አይደለም፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 3ር ቁጥር 22
“በአካል ሦስት "ህላዌ" በመለኮት አንድ ህላዌ ነው”።
በእርግጥም "ሦስት ለሚሆን አምላክ፣ ሦስት ቅዱስ፣ ሦስት ልዑላን፣ ሦስት ጌቶች፣ ሦስት ነገሥታት፣ ሦስት ገዢዎች" ብላችሁ ካስተማራችሁ በግልጽ መድብለ አማልክታውያን ናችሁ፦
፨ሰይፈ ሥላሴ ዘሐሙስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 22-23
“ሦስት ልዑላን ገዢዎች፥ ሦስት ጌቶች ናቸው”።
፨ ሰይፈ ሥላሴ ዘሐሙስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 26
“ሦስት ነገሥታት አንድ አገዛዝ ናቸው”።
፨ ሰይፈ ሥላሴ ዘረቡዕ ምዕራፍ 4 ቁጥር 52
“እነዚህ ገዢዎች በገጽ ሦስት በፈቃድ አንድ ናቸው”።
"ገጽ" ማለት "ፊት" ማለት ነው፥ ባለ ሦስት ፊት አምላክ የዐረማውያን እንጂ የአብርሃም አምላክ በፍጹም አይደለም፦
ሰይፈ ሥላሴ ዘሐሙስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 24
"ሦስት ገጽ አንድ አመለካከት ናቸው"።
ሥላሴ አካላቸው የተለያዩ ከሆኑ አካላቸው አንድ ዓይነት ወይስ የተለያየ? አንድ ዓይነት ከሆነ ምን ዓይነት አንድ ዓይነት? ከተለየስ ምን ዓይነት የተለየ አካል ነው? ገጽታቸውን ሦስት አርጎ ያለያየ ምን ዓይነት ገጽታ ይሆን? "መለኮት ሦስትም አንድም ነው" ማለት የጤና አይደለም፦
ሰይፈ ሥላሴ ዘቀዳሚት ምዕራፍ 7 ቁጥር 68
"ለመለኮት ሦስትነት ምስጋና ይገባል"።
ሰይፈ ሥላሴ ዘቀዳሚት ምዕራፍ 7 ቁጥር 69
"ለመለኮት አንድነት ምስጋና ይገባል"።
ገድለ ተክለ ሃይማኖት 60(61)፥12
"የመለኮት ሦስትነት መቆፈሪያ ልቡን በኮሰተረው እና በቆፈረው ጊዜ"።
በምድር ላይ ያለው እያንዳንዱ ሰው የራሱ ገጽ ያለው ሲሆን በስም፣ በአካል፣ በግብር ስምንት ቢልዮን ነው፥ ግን የሁሉም ምንነት አንድ ምንነት ስለሆነ ስምንት ቢልዮን ሰው አንድ ሰው አይባልም። ስምንት ቢልዮን ሰዎች ያሰኘው በማንነት እከሌ እየተባለ ስለሚለያይ ነው፥ አምላክ በማንነት እከሌ እየተባለ በስም፣ በአካል፣ በግብር ከተለያየ አንድ ሳይሆን ብዙ ነው። በሦስት ፊቶች የተለያየ መለኮት፣ ጌታ፣ ንጉሥ፣ አምላክ እና ፈጣሪ መድብለ አማልክት እንጂ ሌላ አይደለም፦
ሰይፈ ሥላሴ ዘእሑድ ምዕራፍ 8 ቁጥር 41
"ሥስት የምትሆን ጌታዬ፣ ንጉሤ፣ አምላኬ፣ ፈጣሪዬ ሆይ! ለአዳራሽህ መብራት ለመመላለሻህም ፀሐይ አትፈልግም"።
መልክአ ሥላሴ ቁጥር 39
“ሥሉስ ቅዱስ ሆይ! የአደም እና የሔዋን "ፈጣሪዎቻቸው" እንደመሆናችሁ የምርኮኞች ነጻ አውጪ የሆነ ኃይላችሁ የጣዖታትን ሐሰተኝነት አጋለጠ"።
ሥላሴ "ፈጣሪዎች" ከተባሉ ስንት ፈጣሪ ሊኖር ነው? እነርሱም በድፍረት፦ "ኤሎሂም" ማለት "አማልክት" ማለት ነውና "አማልክት" የተባለው ሥላሴን አምልካች ነው" በማለታቸው ሥላሴ "አማልክት" መሆናቸው በግልጽ ነግረውናል። ሳያቅማሙም "ሦስት በአንድ የሆነ አምላክ"Triune God" ይሉታል፣ በአገራችን "ሥላሴ" ማለት "ሦስትነት" ማለት ነው፣ በዐረብ ክርስቲያኖች ዘንድ "ተሥሊስ" تَسْلِيث ይሉታል። በፕሮቴስታንት ዘንድ ደግሞ፦ "አብ እራሱን የቻለ አእምሮ፣ ፈቃድ እና ስሜት አለው፣ ወልድ እራሱን የቻለ አእምሮ፣ ፈቃድ እና ስሜት አለው፣ መንፈስ ቅዱስ እራሱን የቻለ አእምሮ፣ ፈቃድ እና ስሜት አለው" ይላሉ፥ ይህ በኦርቶዶክስ ሦስት አማልክት ነው፦
መጽሐፈ ሜላድ 6፥38 ሦስት ልብ፣ ሦስት ቃል፣ ሦስት እስትንፋስ የሚል ግን ሦስት አማልክት አመለከ"።
"ለበወ" ማለት "አወቀ" ማለት ከሆነ ሦስቱ ማንንነቶች የየራሳቸው ዕውቀት ካላቸው እና እርስ በእርስ የሚነጋገሩ ከሆነ ሦስት ልብ ይሆናል፥ በፕሮቴስታንት ልክ እንደ አርጌናሳውያን አብ ወልድን እና መንፈስ ቅዱስን የሚገዛቸው አስተዳዳሪያቸው ነው፦
1ኛ ቆሮንቶስ 15፥28 አዲሱ መደበኛ ትርጉም ማብራሪያ፦ "ወልድ ለአብ የሚገዛው በአስተዳደር ረገድ ሲሆን..በሥላሴ አካላት መካከል አብ የበላይ አስተዳዳሪ ነው"
እንግዲህ ሥላሴ ሰው በማመኑ የሚድንበት እና በመካዱ የሚጠፋበት አንቀጸ እምነት ቢሆን ኖሮ ነቢያት እና ሐዋርያት በግልጽ ልክ እንደ ተውሒድ ያስቀምጡልን ነበር። ነገር ግን በግልጠተ መለኮት ውስጥ የሥላሴ አሳቡ ስለሌለ «ሦስት ነው» አትበሉ! ተከልከሉ! ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና፡፡ አሏህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፦
4፥171 «ሦስት ነው» አትበሉ! ተከልከሉ! ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና፡፡ አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ وَلَا تَقُولُوا ثَلَاثَةٌ ۚ انتَهُوا خَيْرًا لَّكُمْ ۚ إِنَّمَا اللَّهُ إِلَـٰهٌ وَاحِدٌ
አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛን ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
ወሠላሙ ዐለይኩም
ሥላሴ