በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

37፥84 ወደ ጌታው "በ-ንጹሕ ልብ” በመጣ ጊዜ የኾነውን አስታውስ፡፡፡ إِذْ جَاءَ رَبَّهُ بِقَلْبٍ سَلِيمٍ

"ቀልብ" قَلْب የሚለው ቃል "ቀለበ" قَلَبَ ማለትም "ለበወ" "ሐለየ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ልብ" "ሐልዮ" ማለት ነው፥ "ልብ" የሚለው የግዕዝ ቃል "ለበወ" ማለትም "አጤነ" "አስተዋለ" "አመዛዘነ" "ዐወቀ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ማጤኛ" "ማስተዋያ" "ማመዛዘኛ" "ማወቂያ" የሚል ፍቺ አለው። "ፉአድ" فُؤَاد ስሜትን"emotion" የያዘ የውስጥ ክፍል ሲሆን "ዐቅል" عَقْل ደግሞ አመክንዮን"intellect" የያዘ የውስጥ ክፍል ነው፥ ፉኣድን እና ዐቅልን አመዛዝኖ የሚይዝ ውሳጣዊ ክፍል "ቀልብ" قَلْب ነው። "ቁሉብ" قُلُوب ደግሞ የቀልብ ብዙ ቁጥር ሲሆን "ልቦች" ማለት ነው፦

15፥51 አላህም "በልቦቻችሁ" ውስጥ ያለውን ሁሉ ያውቃል፡፡ አላህም ዐዋቂ ታጋሽ ነው፡፡ وَاللَّهُ يَعْلَمُ مَا فِي قُلُوبِكُمْ ۚ وَكَانَ اللَّهُ عَلِيمًا حَلِيمًا

"ነፍሥ" نَفْس ማለት "እራስነት"own self" ማለት ሲሆን አንፉሥ" أَنْفُس የነፍሥ ብዙ ቁጥር ነው፥ ነፍሥ በሰው ውስጥ ያለውን ልብ ለማመልከት ይመጣል፦

2፥284 በ"ነፍሶቻችሁ" ውስጥ ያለውን ብትገልጹ ወይም ብትደብቁት አላህ በእርሱ ይቆጣጠራችኋል"፡፡ وَإِن تُبْدُوا مَا فِي أَنفُسِكُمْ أَوْ تُخْفُوهُ يُحَاسِبْكُم بِهِ اللَّهُ ۖ

"ቁሉቢኩም" قُلُوبِكُمْ የሚለው "አንፉሢኩም" أَنفُسِكُمْ በሚል ተለዋዋጭ ከመጣ ዘንዳ ቀልብ ወይም ነፍስ ውስጥ ያለው ሀብት እውነተኛ ሀብት ሲሆን ይህም ውሳጣዊ ሀብት ነው፦

ሶሒሕ ኢብኑ ሒባን መጽሐፍ 1 ሐዲስ 3055
አቢ ሁረይራህ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "ሀብት በውጪ አይኖርም፥ እውነተኛ ሀብት የነፍሥ ሀብት ብቻ ነው"። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ عَنْ رَسُولِ اللهِ صَلى الله عَلَيه وسَلم أَنَّهُ قَالَ لَيْسَ الْغِنَى عَنْ ظَهْرٍ إِنَّمَا الْغِنَى غِنَى النَّفْسِ
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 81, ሐዲስ 35
አቢ ሁረይራህ”ረ.ዐ” እንደተረከው ነቢዩም”ﷺ” አሉ፦ "ሀብት ማለት መጠነ ሰፊ ንብረት መያዝ አይደለም፥ ነገር ግን ሀብት ማለት የነፍሥ ሀብት ነው። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ “‏ لَيْسَ الْغِنَى عَنْ كَثْرَةِ الْعَرَضِ، وَلَكِنَّ الْغِنَى غِنَى النَّفْسِ ‏”‌‏.‏

የውስጥ ሀብት እምነት፣ እሳቤ፣ አሳብ፣ የአስተሳሰብ ቅኝነት፣ ጥልቅ አመለካከት፣ ዕውቀት ነው፥ የውስጥ ድህነት ክህደት፣ ጭፍንነት፣ ጸለምተኝነት፣ ድንቁርና፣ መሃይምነት ነው። እውነተኛ ሀብትም ሆነ ድህነት በልብ ውስጥ ያለ ነው፦

አል-ሙዕጀመል ከቢር መጽሐፍ 4, ሐዲስ 154
አቢ ዘር እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "አቢ ዘር ሆይ! "የተትረፈረፈ ገንዘብ ሀብት ነው" ትላለህን? እኔም፦ "አዎ" አልኩኝ፥ እርሳቸውም፦ "የገንዘብ አለመኖር ድህነት ነው" ትላለህን? እኔም፦ "አዎ" አልኩኝ፥ እርሳቸውም ይህንን ሦስት ጊዜ ደጋገሙት። ከዚያም "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ"፦ "ሀብት በልብ ውስጥ ነው፥ ድህነትም በልብ ውስጥ ነው" አሉ"። عن أبي ذر قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ يَا أَبَا ذَرٍّ تَقُولُ كَثْرَةُ الْمَالِ الْغِنَى قُلْتُ نَعَمْ قَالَ تَقُولُ قِلَّةُ الْمَالِ الْفَقْرُ قُلْتُ نَعَمْ قَالَ ذَلِكَ ثَلاثًا ثُمَّ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ الْغِنَى فِي الْقَلْبِ وَالْفَقْرُ فِي الْقَلْبِ.

መጥፎ ሥራ የሚያሠራን ከልብ የተቀመጠው እውነተኛ ድህነት ነው፥ መልካም ሥራ የሚያሠራን ከልብ የተቀመጠው እውነኛው ሀብት ነው። አምላካችን አሏህ የሚመለከተው ልባችንን እና ሥራችንን እንጂ ቅርጻችንን እና ገንዘባችንን አይደለም፦

ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 45, ሐዲስ 42
አቢ ሁረይራህ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛ"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "አሏህ ወደ ቅርጻችሁ እና ገንዘባችሁ አይመለከትም፥ ነገር ግን ወደ ልባችሁ እና ሥራችሁ ይመለከታል"፡፡ عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ "‏ إِنَّ اللَّهَ لاَ يَنْظُرُ إِلَى صُوَرِكُمْ وَأَمْوَالِكُمْ وَلَكِنْ يَنْظُرُ إِلَى قُلُوبِكُمْ وَأَعْمَالِكُمْ ‏"‏

ልብ የምንነይትበት የኒያህ መቀመጫ ነው፥ ሥራ የሚለካው በኒያህ ስለሆነ ሥራችን የልባችን ውጤት ነው። ጽድቅ መልካም ሥነ ምግባር"ethics" ሲሆን በግልጠተ መለኮት በኩል ከሥነ መለኮት የሚመጣ ነው፥ በተቃራኒው ኃጢአት በልብህ ውስጥ የሚሸረብ ነው፦

ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ, 45, ሐዲስ 16
አን ነዋሥ ኢብኑ ሠዕማል አል አንሷሪይ እንደተረከው፦ "እኔም "የአሏህ መልእክተኛ"ﷺ" ስለ ጽድቅ እና ኃጢአት ጠየኳቸው፥ እርሳቸውም፦ "ጽድቅ መልካም ሥነ ምግባር ነው፥ ኃጢአት በልብህ ውስጥ የሚሸረብ ነው" አሉ"። عَنِ النَّوَّاسِ بْنِ سَمْعَانَ الأَنْصَارِيِّ، قَالَ سَأَلْتُ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم عَنِ الْبِرِّ وَالإِثْمِ فَقَالَ ‏ "‏ الْبِرُّ حُسْنُ الْخُلُقِ وَالإِثْمُ مَا حَاكَ فِي صَدْرِكَ ‏"‏ ‏.‏
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ, 45, ሐዲስ 17
አን ነዋሥ ኢብኑ ሠዕማል አል አንሷሪይ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "ጽድቅ መልካም ሥነ ምግባር ነው፥ ኃጢአት በነፍስ ውስጥ የሚሸረብ ነው"። عَنِ النَّوَّاسِ بْنِ سَمْعَانَ الأَنْصَارِيِّ، قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ "‏ الْبِرُّ حُسْنُ الْخُلُقِ وَالإِثْمُ مَا حَاكَ فِي نَفْسِكَ ‏"‏ ‏

"ልብ" እና "ነፍስ" በአንድ ዐውድ ላይ ተለዋዋጭ ቃል ሆኖ መምጣቱ በራሱ ነፍስ ውሳጣዊ ልብን ያመለክታል፥ ልብ ይህን ያክል በሰው ሕይወት ላይ አውንታዊ ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው። ጀነት ወደ አሏህ በንጹሕ ልብ ለመጣ ትቀረባለች፥ ለምሳሌ፦ ኢብራሂም ወደ ጌታው በንጹሕ ልብ የመጣ ሰው ነው፦

50፥33 አልረሕማንን በሩቁ ኾኖ ለፈራ እና "በ-ንጹሕ ልብ" ለመጣ ትቀረባለች፡፡ مَّنْ خَشِيَ الرَّحْمَـٰنَ بِالْغَيْبِ وَجَاءَ بِقَلْبٍ مُّنِيبٍ
37፥84 ወደ ጌታው "በ-ንጹሕ ልብ” በመጣ ጊዜ የኾነውን አስታውስ፡፡፡ إِذْ جَاءَ رَبَّهُ بِقَلْبٍ سَلِيمٍ
26፥89 ወደ አላህ "በ-ንጹሕ ልብ" የመጣ ሰው ቢኾን እንጂ፡፡ إِلَّا مَنْ أَتَى اللَّهَ بِقَلْبٍ سَلِيمٍ

እነዚህ አናቅጽ ላይ "ንጹሕ" ተብሎ የተቀመጠው ቃል "ሠሊም" سَلِيم ነው፥ አንድ በኢሥላም ልቡን ሢያሠልም ልቡ ውስጥ "ሠላም" سَلَام ስላለ ልቡ ሠሊም ስትሆን እርሱ ደግሞ "ሣሊም" سَالِم‎ ይሆናል፦

ኢማም አሕመድ መጽሐፍ 1, ሐዲስ 17027
ዐምር ኢብኑ ዐባሣህ እንደተረከው፦ "አንድ ሰው የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" ሆይ! ኢሥላም ምንድን ነው? ብሎ ጠየቀ፥ እርሳቸውም"ﷺ"፦ "ልብህን ለአሏህ ዐዘ ወጀል ማሥለም ነው" አሉት"። عَنْ عَمْرِو بْنِ عَبَسَةَ قَالَ قَالَ رَجُلٌ يَا رَسُولَ اللَّهِ مَا الْإِسْلَامُ قَالَ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ أَنْ يُسْلِمَ قَلْبُكَ لِلَّهِ عَزَّ وَجَلَّ

አንድ ሰው ልቡን ለአሏህ ካሠለመ ጀነት ይገባል፥ ልቡን ለአሏህ ያሠለመ ሰው ከጀሀነም ይድናል፦

አል አደቡል ሙፍረድ መጽሐፍ 1, ሐዲስ 260
አቢ ሁረይራህ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛ"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "ነፍሴ በእጁ በሆነው እምላለው፥ እስካልሠለማችሁ ድረስ ጀነት አትገቡም"። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ‏:‏ وَالَّذِي نَفْسِي بِيَدِهِ، لاَ تَدْخُلُوا الْجَنَّةَ حَتَّى تُسْلِمُوا
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 12, ሐዲስ 163
ዐምር ኢብኑ አል ዓስ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛ"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "የሠለመ ዳነ"። عَنْ عَمْرِو بْنِ الْعَاصِ أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ "‏ قَدْ أَفْلَحَ مَنْ أَسْلَمَ ‏"‏ ‏.‏

አምላካችን አሏህ በልባችን ውስጥ ያለውን እውነተኛ ሀብት እንድንጠቀም ይርዳን! በሠሊም ቀልብ ወደ እርሱ የምንመጣ ያድርገን! አሚን።

✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ

ወሠላሙ ዐለይኩም
ሥነ ፍጥረት