በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
” إِنَّهُ لَقَوْلُ رَسُولٍ كَرِيمٍ * وَمَا هُوَ بِقَوْلِ شَاعِرٍ قَلِيلًا مَا تُؤْمِنُونَ * وَلَا بِقَوْلِ كَاهِنٍ قَلِيلًا مَا تَذَكَّرُونَ * تَنْزِيلٌ مِنْ رَبِّ الْعَالَمِينَ ”
እርሱ (ቁርኣን) የተከበረ መልክተኛ ቃል ነው፡፡ እርሱም የባለቅኔ ቃል (ግጥም) አይደለም ጥቂትን ብቻ ታምናላችሁ። የጠንቋይም ቃል አይደለም ጥቂቱን ብቻ ታስታውሳላችሁ። ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው
إِنَّهُ لَقَوْلُ رَسُولٍ كَرِيمٍ * ذِي قُوَّةٍ عِنْدَ ذِي الْعَرْشِ مَكِينٍ * مُطَاعٍ ثَمَّ أَمِينٍ
እርሱ (ቁርኣን) የክቡር መልክተኛ ቃል ነው፡፡ የኃይል ባለቤት፡ በዙፋኑ ባለቤት ዘንድ ባለሟል የሆነ፡፡ በዚያ ስፍራ ትዕዛዙ ተሰሚ ታማኝ የሆነ (መልክተኛ ቃል) ነው፡፡
ከነዚህ ሁለት የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች በመነሳት አንዳንድ ክርስቲያን ወገኖች ቁርኣን የጂብሪል (ዐለይሂ ሰላም) ቃል እንጂ የአላህ አይደለም ይሉናል፡፡ እኛም ለቀረቡት የቅዱስ ቁርኣን ጥቅሶች ምላሻችንን ከመስጠታችን በፊት አንድ ጥያቄ እናቅርብላቸው፡፡ እሱም፡- ባቀረባችሁት ሁለት የቁርኣን ጥቅሶች መሰረት፡ ቅዱስ ቁርኣን የጂብሪል ቃል ነው ብላችሁ ስትሞግቱን፡ እናንተ የጂብሪል ቃል መሆኑን አምናችሁ ተቀብላችሁ ነውን? ወይስ እንዲሁ ሳታምኑበት ለሙግት ብቻ?
አዎ የጂብሪል ቃል ነው! ብለን እናምናለን ካላችሁ፡ እንግዲያውስ መልአኩ ጂብሪል አይዋሽምና በቃሉ ውስጥ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ መልክተኛና የነቢያት መደምደሚያ መሆናቸውን መስክሯል (ሱረቱል-አሕዛብ 40)፡፡ ስለዚህ እናንተም መልአኩ ባለው መሰረት ለምን በሳቸው ነቢይነት አታምኑም?
አይ እኛ በነቢዩ ሙሐመድ ነቢይነት አናምንም፡፡ ቁርኣንም የጂብሪል ቃል ነው ብለን አንቀበልም! ከሆነ ምላሻችሁ፡ እንግዲያውስ ከቁርኣን ውስጥ ጥቅስ አውጥቶ ማስረጃ መጠቀሙ ለምን አስፈለገ? እኛ ሙስሊሞች ከመጽሐፋችሁ ውስጥ ጥቅስ መዝዘን ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን የሚያመላክት ጥቅስ ብናሳያችሁ ፡ ነቢይ መሆኑን ስላመንን ነው እንጂ ለጭቅጭቅ አይደለም፡፡ ታዲያ የናንተን ከቁርኣን ጥቅስ መምዘዝ ምን እንበለው? እንዲሁ ግራ ለማጋባት? ወይስ የናንተ መጽሐፍ ላይ ጥያቄ እንዳናበዛና በራሳችን እምነት ላይ ለሚነሳው ጥያቄ ብቻ መልስ መስጠቱ ላይ እንድንጠመድ? ለማንኛውም ጉዳዩን ለህሊና እንተወውና ወደ ትክክለኛ ፍቺውና ማብራሪያ እንግባ፡-
ቅዱስ ቁርኣን ከሱረቱል-ፋቲሓ እስከ ሱረቱ-ናስ ያለው 114ቱም ሱራ የአላህ ቃል ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩት ቃላት በጠቅላላ የአላህ ናቸው፡፡ ቃሉም መልእክቱም የራሱ ነው፡፡ የመላእክት፣ የነቢያትና የተራ ምእመኖች ሀሳብ ጣልቃ አልገባበትም፡ አይገባበትምም፡፡ ሁሌም ቃሉን ስናስተምርም ሆነ ስንማር የምንሰማው ‹አላህ እንዲህ አለ› የሚል እንጂ፡ ‹እንትና እንዲህ አለ› ሲባል አይደለም፡፡ ከላይ የቀረቡትም ሁለት የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች ከዚሁ ሀሳብ ጋር የሚስማሙ እንጂ የሚጣረሱ አይደሉም፡፡ ዝርዝር ሃሳባቸውንም በኋላ ላይ እንመለስበታለን፡፡ ቅዱስ ቁርኣን ከአላህ ዘንድ የመጣ የራሱ የአላህ ቃል መሆኑን የሚያመላክቱ ብዙ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ጥቂቱን እንመልከተው፡-
1. በቀጥታ የአላህ ንግግር መባሉ፡-
አንዱና ዋነኛው ማስረጃችን ነው፡፡ በቀጥታና ግልጽ በሆነ መልኩ ቁርኣን የአላህ ቃል እንደሆነ እራሱ ቁርኣን ይነግረናል፡፡ እንዲህ ይላል፡-
وَإِنْ أَحَدٌ مِنَ الْمُشْرِكِينَ اسْتَجَارَكَ فَأَجِرْهُ حَتَّى يَسْمَعَ كَلَامَ اللَّهِ ثُمَّ أَبْلِغْهُ مَأْمَنَهُ ذَلِكَ بِأَنَّهُمْ قَوْمٌ لَا يَعْلَمُونَ
ከአጋሪዎችም አንዱ ጥገኝነትን ቢጠይቅ የአላህን ቃል ይሰማ ዘንድ አስጠጋው፤ ከዚያም ወደ መጠበቂያዉ ስፍራ አድርሰው፤ ይህ እነሱ የማያዉቁ ሕዝቦች በመሆናቸው ነው።
2. ከሱ ዘንድ መባሉ፡-
በብዙ የቁርኣን ክፍሎች ላይ ቁርኣን ለነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የተሰጠው ከጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) ሳይሆን ከአላህ ዘንድ መሆኑን በመግለጽ፡ የቃሉ ባለቤት አላህ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ የጂብሪል ቃል ቢሆን ኖሮ ‹ከሱ ዘንድ› መሆኑን የሚያመላክት አንድ ጥቅስ እንኳ ባገኘን ነበር፡፡ ግን የለም፡ ሊኖርም አይችልም፡፡
وَإِنَّكَ لَتُلَقَّى الْقُرْآنَ مِنْ لَدُنْ حَكِيمٍ عَلِيمٍ
አንተም ቁርኣንን ጥበበኛና ዐዋቂ ከሆነው (ጌታህ) ዘንድ በእርግጥ ትሠጣለህ።
“እንደዚሁ በእርግጥ ካለፉት ወሬዎች ባንተ ላይ እንተርካለን፤ ከኛም ዘንድ ቁርኣንን በእርግጥ ሰጠንህ።” (ሱረቱ ጣሀ 99)፡፡
3. የመጽሐፉ መወረድ ከአላህ ነው መባሉ፡-
ቅዱስ ቁርኣን ከአላህ ዘንድ ወደ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ልብ የተወረደ ነው በማለት ይገልጻል፡-
الم • تَنْزِيلُ الْكِتَابِ لَا رَيْبَ فِيهِ مِنْ رَبِّ الْعَالَمِينَ
አ. ለ. መ. ( አሊፍ ላም ሚም)። የመጽሐፉ መወረድ ጥርጥር የለበትም፤ ከዓለማት ጌታ ነው።
“የመጽሐፉ መወረድ፣ አሸናፊውና ጥበበኛ ከሆነው አላህ ነው።” (ሱረቱ-ዙመር 1)፡፡