በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ቁርኣን 15፥2 እነዚያ የካዱት በትንሣኤ ቀን ሙሥሊሞች በኾኑ ኖሩ በብዛት ይመኛሉ፡፡
رُّبَمَا يَوَدُّ الَّذِينَ كَفَرُوا لَوْ كَانُوا مُسْلِمِينَ

"ሙሥሊም" مُسْلِم የሚለው ቃል "አሥለመ" أَسْلَمَ ማለትም "ታዘዘ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ታዛዥ" ማለት ነው፥ የሙሥሊም ብዙ ቁጥር ደግሞ "ሙሥሊሙን" مُّسْلِمُون ወይም "ሙሥሊሚን" مُسْلِمِين ሲሆን "ታዛዦች" ማለት ነው፦

ቁርኣን 21፥108 «ያ ወደ እኔ የሚወረደው፦ “አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው” ማለት ነው፥ ታዲያ እናንተ ፍጹም ታዛዦች ናችሁን» በላቸው፡፡
قُلْ إِنَّمَا يُوحَىٰ إِلَيَّ أَنَّمَا إِلَـٰهُكُمْ إِلَـٰهٌ وَاحِدٌ ۖ فَهَلْ أَنتُم مُّسْلِمُون

እዚህ አንቀጽ ላይ "ታዛዦች" ለሚለው የገባው ቃል "ሙሥሊሙን" مُّسْلِمُون ሲሆን "ሙሥሊም" مُسْلِم ማለት "አንዱን አምላክ በብቸኝነት የሚያመልክ ወይም የሚታዘዝ" ማለት ነው፥ የፈጠረንን አሏህን በሙፍረዳት እና በሙሐረማት ወይንም በአምስቱ ሙሐከማት ስንታዘዝ ሙሥሊም እንሰኛለን። አምላካችን አሏህ ወደ አደም ኪዳን ሲያወርድ "ሙሥሊሞች" ብሎ ጠራን፦

ቁርኣን 20፥115 ወደ አደምም ከዚህ በፊት ኪዳንን በእርግጥ አወረድን፡፡
وَلَقَدْ عَهِدْنَا إِلَىٰ آدَمَ مِن قَبْلُ
ቁርኣን 22፥78 በአላህም ሃይማኖት ተገቢውን ትግል ታገሉ፡፡ እርሱ መርጧችኋል፡፡ በእናንተም ላይ በሃይማኖቱ ውስጥ ምንም ችግር አላደረገባችሁም፡፡ የአባታችሁን የኢብራሂምን ሃይማኖት ተከተሉ፡፡ እርሱ ከዚህ በፊት ሙሥሊሞች ብሎ ሰይሟችኋል፡፡
وَجَاهِدُوا فِي اللَّهِ حَقَّ جِهَادِهِ ۚ هُوَ اجْتَبَاكُمْ وَمَا جَعَلَ عَلَيْكُمْ فِي الدِّينِ مِنْ حَرَجٍ ۚ مِّلَّةَ أَبِيكُمْ إِبْرَاهِيمَ ۚ هُوَ سَمَّاكُمُ الْمُسْلِمِينَ مِن قَبْلُ

ቁርኣን በወረደበት ጊዜ አሏህ፦ "ሚን ቀብሉ" مِن قَبْلُ ማለትም "ከዚህ በፊት" የሚለውን ኢሥሙል መጅሩር የሚጠቁመን ወደ አደም ወሕይን ያወረደበትን ጊዜ ነው፥ በዚያን ጊዜ "ሙስሊሞች" ብሎ ሰይሟል። "እርሱ" የሚለው ተውላጠ ስም "አሏህ" የሚለውን ስም ተክቶ የመጣ ስለሆነ "ሙስሊሞች" ብሎ የሰየመው ኢብራሂም ሳይሆን አሏህ ነው፥ ምክንያቱም ከኢብራሂም በፊት ኑሕ፦ "ከሙሥሊሞች" እንደሆነ ተናግሯል፦

ቁርኣን 10፥72 «ብትሸሹም አትጎዱኝም፡፡ ከምንዳ ምንንም አልለምናችሁምና፥ ምንዳዬ በአላህ ላይ እንጂ በሌላ ላይ አይደለም፡፡ ከሙሥሊሞች እንድሆንም ታዝዣለሁ፡፡»
فَإِن تَوَلَّيْتُمْ فَمَا سَأَلْتُكُم مِّنْ أَجْرٍ ۖ إِنْ أَجْرِيَ إِلَّا عَلَى اللَّهِ ۖ وَأُمِرْتُ أَنْ أَكُونَ مِنَ الْمُسْلِمِينَ

ከኑሕ በኃላ ኢብራሂም ከልጁ ከኢሥማዒል ጋር፦ "ሙሥሊሞች አርገን" ብሎ ዱዓእ አርጓል፦

ቁርኣን 2፥128 ጌታችን ሆይ! ለአንተ ታዛዦችም አድርገን፡፡ ከዘሮቻችንም ለአንተ ታዛዦች ሕዝቦችን አድርግ፡፡
رَبَّنَا وَاجْعَلْنَا مُسْلِمَيْنِ لَكَ وَمِن ذُرِّيَّتِنَا أُمَّةً مُّسْلِمَةً لَّكَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ታዛዦች" ለሚለው የገባው ቃል "ሙሥሊማህ" مُّسْلِمَة መሆኑ በራሱ ሙሥሊም ማለት ለአሏህ ታዛዥ መሆኑን ቁልጭ አርጎ አያሳይምን? አሏህ ኢብራሂምን፦ "አሥሊም" أَسْلِمْ ባለው ጊዜ "አሥለምቱ" أَسْلَمْتُ አለው፦

ቁርኣን 2፥131 ጌታው ለእርሱ ታዘዝ ባለው ጊዜ ለዓለማት ጌታ ታዘዝኩ አለ፡፡
إِذْ قَالَ لَهُ رَبُّهُ أَسْلِمْ ۖ قَالَ أَسْلَمْتُ لِرَبِّ الْعَالَمِينَ

ኢብራሂም ልጆቹን ኢሥማዒልን እና ይስሓቅን እንዲሁ የልጅ ልጁን የዕቁብን በኢሥላም አዘዘ፦

ቁርኣን 2፥132 በእርሷም ኢብራሂም ልጆቹን አዘዘ፡፡
وَوَصَّىٰ بِهَا إِبْرَاهِيمُ بَنِيهِ

ከዚያም የዕቁብም ልጆቹን፦ "እናንተ ሙሥሊሞች ኾናችሁ እንጂ አትሙቱ" አላቸው፦

ቁርኣን 2፥132 የዕቁብም፦ «ልጆቼ ሆይ! አላህ ለእናንተ ሃይማኖትን መረጠ፤ ስለዚህ እናንተ ሙሥሊሞች ኾናችሁ እንጂ አትሙቱ» አላቸው፡፡
وَيَعْقُوبُ يَا بَنِيَّ إِنَّ اللَّهَ اصْطَفَىٰ لَكُمُ الدِّينَ فَلَا تَمُوتُنَّ إِلَّا وَأَنتُم مُّسْلِمُونَ

ሙሣም ለሕዝቦቹ፦ "ሙሥሊሞች እንደ ሆናችሁ በአሏህ ላይ ትመካላችሁ" አላቸው፦

ቁርኣን 10፥84 ሙሣም አለ፡- «ሕዝቦቼ ሆይ! በአላህ አምናችሁ እንደ ሆነ በርሱ ላይ ተጠጉ፡፡ ታዛዦች እንደ ሆናችሁ በአላህ ላይ ትመካላችሁ»።
وَقَالَ مُوسَىٰ يَا قَوْمِ إِن كُنتُمْ آمَنتُم بِاللَّهِ فَعَلَيْهِ تَوَكَّلُوا إِن كُنتُم مُّسْلِمِينَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ታዛዦች" ለሚለው የገባው ቃል "ሙሥሊሚን" مُّسْلِمِين እንደሆነ ልብ አድርግ! የዒሣ ሐዋርያትም ለዒሣ፦ "ሙሥሊሞች መኾናችንን መስክር" ማለታቸው በራሱ ከጥንትም የነበሩት ነቢያት እና ሐዋርያት ሙሥሊሞች ነበሩ፦

ቁርኣን 3፥52 ሐዋርያት፡- «እኛ የአላህ ረዳቶች ነን፤ በአላህ አምነናል፤ እኛም ትክክለኛ "ታዛዦች" መኾናችንን መስክር» አሉ፡፡
قَالَ الْحَوَارِيُّونَ نَحْنُ أَنصَارُ اللَّهِ آمَنَّا بِاللَّهِ وَاشْهَدْ بِأَنَّا مُسْلِمُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ታዛዦች" ለሚለው የገባው ቃል "ሙሥሊሙን" مُسْلِمُون መሆኑን ልብ አልክን? እንግዲህ ስለ ሉጥ፣ ዩሡፍ፣ ሡለይማን ወዘተ ነቢያት ሁሉ ሙሥሊሞች መሆናቸውን የጊዜ እና የቦታ ጉዳይ እንጂ በቁና ጥቅስ ማቅረብ ይቻላል።
በጥቅሉ ከቁርኣን መውረድ በፊት አንዱን አምላክ የሚያመልኩ የነበሩት ሙዋሒዱን በእነርሱ ላይ ቁርኣን በሚነበብላቸውም ጊዜ፦ "እኛ ከቁርኣን በፊት ሙሥሊሞች ነበርን" ሲሉ ጥንት ነቢያት እና ሐዋርያት ሲያመልኩት የነበረውን አንዱን አምላክ አምላኪ መሆናቸውን ማሳያ ነው፦

ቁርኣን 27፥53 በእነርሱ ላይ በሚነበብላቸውም ጊዜ «በእርሱ አምነናል፡፡ እርሱ ከጌታችን የኾነ እውነት ነው፡፡ እኛ ከእርሱ በፊት ሙሥሊሞች ነበርን» ይላሉ፡፡
وَإِذَا يُتْلَىٰ عَلَيْهِمْ قَالُوا آمَنَّا بِهِ إِنَّهُ الْحَقُّ مِن رَّبِّنَا إِنَّا كُنَّا مِن قَبْلِهِ مُسْلِمِينَ
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 15, ሐዲስ 457
ኢብኑ ዐባሥ እንደተረከው፦ "ነቢዩ"ﷺ" በረውሓእ ጋላቢዎችን በማግኘት፦ "እናንተ ማን ናችሁ? ብለው ጠይቋቸው፥ እነርሱም "እኛ ሙሥሊሞች ነን" ብለው መለሱላቸው። እነርሱም አንተስ ማን ነህ አሏቸው "እሳቸውም፦ "እኔ የአሏህ መልዕክተኛ ነኝ" አሏቸው"።
عَنِ ابْنِ عَبَّاسٍ، عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم لَقِيَ رَكْبًا بِالرَّوْحَاءِ فَقَالَ ‏"‏ مَنِ الْقَوْمُ ‏"‏ ‏.‏ قَالُوا الْمُسْلِمُونَ ‏.‏ فَقَالُوا مَنْ أَنْتَ قَالَ ‏"‏ رَسُولُ اللَّهِ ‏"‏

አምላካችን አሏህ በፍርድ ቀን እነዚያ በአንቀጾቹ ያመኑ እና ሙሥሊሞች የነበሩትን፦ "ገነትን ግቡ! እናንተም ጥንዶቻችሁም ትደሰታላችሁ ትከበሩማላችሁ" ይላቸዋል፦

ቁርኣን 43፥69 እነዚያ በአንቀጾቻችን ያመኑና ፍጹም ታዛዦች የነበሩትን «ገነትን ግቡ! እናንተም ጥንዶቻችሁም ትደሰታላችሁ ትከበሩማላችሁ» ይባላሉ፡፡
الَّذِينَ آمَنُوا بِآيَاتِنَا وَكَانُوا مُسْلِمِينَ ادْخُلُوا الْجَنَّةَ أَنتُمْ وَأَزْوَاجُكُمْ تُحْبَرُونَ
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 1, ሐዲስ 212
አቢ ሁረይራህ"ረ.ዐ." እንደተረከው፦ "ነቢዩ"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "እነሆ ሙሥሊም የሆነች ነፍስ እንጂ ሌላው ጀነትን አይገባትም"።
ﻋَﻦْ ﺃَﺑِﻲ ﻫُﺮَﻳْﺮَﺓَ، ﺭﺿﻲ ﺍﻟﻠﻪ ﻋﻨﻪ ﻗَﺎﻝ ﻋﻦ ﺍﻟﻨَّﺒِﻲّ ﺻَﻠَّﻰ ﺍﻟﻠﻪُ ﻋَﻠَﻴْﻪِ ﻭَﺳَﻠَّﻢَ ﺃﻧﻪ ﻗَﺎﻝَ ﺃَﻧَّﻪُ ﻟَﺎ ﻳَﺪْﺧُﻞُ ﺍﻟْﺠَﻨَّﺔَ ﺇِﻟَّﺎ ﻧَﻔْﺲٌ ﻣُﺴْﻠِﻤَﺔٌ

በተቃራኒው ከሃድያን በፍርዱ ቀን ሙሥሊሞች በኾኑ ኖሩ በብዛት ይመኛሉ፦

ቁርኣን 15፥2 እነዚያ የካዱት በትንሣኤ ቀን ሙሥሊሞች በኾኑ ኖሩ በብዛት ይመኛሉ፡፡
رُّبَمَا يَوَدُّ الَّذِينَ كَفَرُوا لَوْ كَانُوا مُسْلِمِينَ

አሏህ እሥልምናን እንደወፈቀን ሙሥሊም አርጎ ያሙተን! አሚን።

✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም